







በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን፣ ዛባ ጋዞ ወረዳ ዳቼ ደነባ ቀበሌ በመንግሥትና በዩኒሴፍ የገንዘብ ድጋፍ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የክልሉ የውሃ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በተገኙበት ተመርቋል።
በወንድማገኝ አየለ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ የተገነባው ይኸው የውሃ ፕሮጀክት 18 ኪሎሜትር የመስመር ጥገና፣ 75 ሺህ ሊተር የውሃ ማጠራቀሚያ እና 9 የውሃ ቦኖ እንዲሁም የከብት ውሃ መጠጫ ያካተተው የዳቼ ደነባ ንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ2 ሺህ 300 በላይ የአከባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚደርግ ሲሆን ከ12 ሚሊዮን ብር የግንባታ ውጪ ወጥተው መገንባቱ ተግልጿል።
የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በአከባቢው ከዚህ በፊት ይከሰት የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው የፕሮጀክቱ ግንባታ እውን እንዲሆን በተለያየ መልኩ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
በክልሉ ምሥረታ ወቀት የነበረው የውሃ ሽፋን አነስተኛ እንደነበረ ያስታወሱት የቢሮው ሃላፊ ይህንን ማየቆ ለመፍታት በተሰጠው ትኩረት በርካታ የውሃ ፕሮጀክቶችን በክልሉ ሁሉም አከባቢ በመገንባት 350 ሺህ ገደማ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
የተገነባ የውሃ ፕሮጀክት ዘላቂ አግልግሎት እንዲሰጥ ተጠቃሚ ማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ መግባት እንዳለበት የጠቆሙት ኢንጂነር በየነ ተጠቃሚው ማህበረሰብ የውሃ አውታሩ ለብልሽት እንዳይደረግ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
በአከባቢው ተጨማሪ ጥናት በማድረግ የውሃ ቦኖ ቃል የገቡት በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ኢንጂነር ጌታቸው አስማሬ የአከባቢው ማህበረሰብ የተገነባውን ቦኖ በጥንቃቄ እንዲጠቀም ጠይቀዋል።
በዞኑ ያለውን አነስተኛ የውሃ ሽፋን ለማሻሻል ከመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ተግባራት አውንታዊ ውጤት መመዝገቡን የገለጹት የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በፕሮጀክቱ ግንባታ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
