
መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበርና ለዜጎች አብሮነት መጎልበት ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበርና ለህዝብ አብሮነት መጠናከር ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡
ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ከመገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅ መሆኑን አንስተው፤ በተቃራኒው አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ለፖለቲካ ፍላጎት መጠቀሚያ ሲውሉ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡
እነዚህ መገናኛ ብዙሃን በሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ግጭት በመፍጠር ከተፈጠረው ግጭት ፖለቲካዊ ትርፍ ማግኘት የሚፈልጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በቸልተኝነትና አቅም ክፍተት የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውንም እንዲሁ፡፡
ባለስልጣኑ የአቅም ክፍተቶችን ለመሙላት የተለያዩ ማኑዋሎችን በማዘጋጀት ስልጠና መስጠቱንም ጠቁመዋል።
ለአብነትም ለግጭት ወቅት ዘገባ ማኑዋል በማዘጋጀት ለጋዜጠኞች እና አርታኢያን ተደራሽ ማድረጉን አንስተዋል፡፡
ከባለስልጣኑ ባሻገር የመገናኛ ብዙሀን ተቋማትም የባለሙያዎቻቸውን የአቅም ክፍተት በሙሙላት ረገድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው ያነሱት፡፡
የሀይማኖት፣ የንግድ እንዲሁም የህዝብ መገናኛ ብዙሀን በስራዎቻቸው የህዝብን አብሮነትና ሰላም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተቃረነ መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴ የሀገርና የህዝብን ጥቅም መቃወም መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በመሰል ተግባራት በሚሳተፉት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
