በጥናትና ምርምር የተደገፉ ውሳኔዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

Spread the love

በጥናትና ምርምር የተደገፉ ውሳኔዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛውን ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

በመርኃ-ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ፣ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና የምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል አፈ-ጉባዔዎች፣ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

በኮንፍረንሱ በምክር ቤቱ ዋና ዋና ተልዕኮዎች በሆኑት በሕግ አወጣጥ፣ በሕዝብ ውክልና፣ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምርና ጥናት ሥራዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

ዛሬ በሚካሄደው ኮንፍረንስ አሥር የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንደሚቀርቡ ተመላክቷል።

ከጥናትና ምርምር ሥራዎች የሚገኙ ምክረ-ኃሳቦችን እንደግብዓት በመጠቀም ምክር ቤቱ የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ትልቅ እገዛ የሚያደርጉ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ፓርላማ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ተቋም ነው።

ምክር ቤቶች የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫዎችና የሕዝብ ውክልና ያላቸው ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በእነዚህ ተቋማት የሚሰጡ ውሳኔዎች ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የሕዝብ ፍላጎትና ጥቅምን መሠረት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቶች ተልዕኳቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች በሳይንሳዊ መረጃና በእውቀት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ በጥናትና ምርምር ሊደገፉ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ይህንን ከግምት በማስገባት ባለፉት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርላማ ሥርዓትን በተሻለ አግባብ መተግበር የሚያስችል በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሥራዎች በጥናትና ምርምር የተደገፉ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በጥናትና ምርምር የተደገፉ ውሳኔዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት 42 የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንደተሰሩ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *