







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች ተቋማትና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ምዕራፍ አንድ (UIIDP 1) ፕሮግራም አፈጻጸም ማጠቃለያ ግምገማ መድረክ በሚዛን አማን ተካሂዷል ።
በመድረክ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ኢንጂነር የማታለም ቸኮል የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊው በከተሞች እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥርን መሸከም የሚያስችል አቅም ያለው ከተማን ለመፍጠር ፕሮግራሙ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
ፕሮግራሙ ላለፋት አምስት ዓመት በሚዛን አማን፣ በቴፒና ቦንጋ ከተሞች የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታትና በከተሞች የማስፈጸም አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት በመስጠት ሲሰራ ቆይቷል ተብለዋል ።
አክለውም አሁን በከተሞች እየታዩ ያሉት የመሠረተ ልማት አውታሮች ተደራሽነት የጥራት መሻሻልና በማስፈፀም አቅም ላይ ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ሚና ፕሮግራሙ እንደተጫወተ ተገልጿል ።
ይሁን እንጂ በከተሞች ላይ ግንባታን በጊዜና በጥራት ከማስፈፀም፣ የግዥ ስርዓቱን ከማስተካከል፣ ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ እንዲሁም ገቢን አሟጥጦ ከማሰባሰብ አንጻር ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ስለሚያስፈልግ ከምዕራፍ አንድ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ማስተካከያ በሚፈልጉት ጉዳዮች ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል ።
በመድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ሀብታሙ ካፒትን የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከተሞች የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ማዕከል በመሆናቸው ከህዝብ የሚመጣውን ፍላጎት በመንግሥት በጀት ብቻ መሸፈን ስለማይቻል ፕሮግራሙ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በማስታወስ በጀቱን ለታለመለት ዓላማ ለማዋልና የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል ።
የአፈጻጸም ሪፖርቱ በክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴ ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን በውይይት መድረክ የከተሞች ተቋማትና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ምዕራፍ አንድ ማጠቃለያ የአፈጻጸም ሪፖርት በክልሉ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ኢታና ለተሳታፊዎች አቀርቧል ።
በሪፖርቱ ከዓለም ባንክ፣ ከዞኖችና ከከተማ አስተዳደር በዕቅድ ተይዞ በጋራ በተገኘው ከ627 ሚለየን ብር በላይ በጀት የመሠረተ ልማትና በከተሞች አቅም ግንባታ ላይ የተለያዩ ተግባራት እንደተከናወኑና ለውጥም እንደታየው ተገልጿል ።
በውይይቱ በከተሞች የመሠረተ ልማት ተደራሽነትና ጥራት እየተሻሻለ መምጣት፣ የሴቶች ተሳትፎ መጨመር፣ የገቢ አሰባሰብ እያደገ መምጣት እና ሌሎች በአቅም ግንባታ ዘርፍ የማስፈጸም አቅም እየጎለበተ መሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተነስቷል ።
በውይይቱ ላይ ማቺንግ ፈንድ በጊዜ ገቢ ያለማድረግ ፣ የመሬት ሀብትን በአግባቡ ከመመዝገብና ከማልማት፣ ወቅታዊ ሪፖርት ያለመላክ፣ የፕሮጀክት አፈጻጸም መዘግየት ፣ በቀጣይ መሻሻል እንዳለበት በሪፖርቱ ላይ ተነስቶ ውይይት ተደርጓል ።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊዎችና የማነጅመንት አካላት እና የክልልና የዞን ስትርንግ ኮሚቴ አባላት እንድሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጌታሁን ግርማ
