
ኢትዮጵያ ሀገራችን ለበርካታ ዘመናት መከላከል ላይ መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ስትተገብር እንደቆየችና በርካታ የሆኑ ለውጦች በጤናው ዘርፍ መመዝገባቸው ይታወሳል ።
ከዚህም መካከል የወባ በሽታን በእጅጉ ለመቀነስ ብሎም ለመቆጣጠር በሚያስችል ደረጃ ላይ ተደርሶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የወባ ስርጭት በስፋት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቅሳሉ ።
ከነዚህም ክልሎች የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንዱ ነው።
የወባ በሽታ በወባ አስተላላፊ ትንኝ ንክሻ ምንክያት የሚመጣ በሽታ ነው። የበሽታው ምልክቶች፣ ትኩሳት፣ብርድ ብርድ ማለት፣ ማላብ፣ራስ ምታት፣ የሰውነት መቆረጣጠም፣ማቅለሽለሽና ማስመለስ ናቸው።
የወባ በሽታ ስርጭት በክልላችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ለመምጣቱ የአየር መዛባት ፣ ለመንገድ መሠረተ ልማት በተቆፈሩ ፣ለማዕድን የተቆፎሩ ቦታዎች፣ በመኖርያ አከባቢ ያቆሩ ውሃን በጊዜ ያለማፍሰስ፣ እንዲሁም በሽታ መከላከል ላይ የሚያተኩረው የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት ላይ መዘናጋት መፈጠሩ ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል ።
በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበሽታውን ስርጭት ፣ የፅኑ ህሙማን ቁጥር ብሎም የሞት መጠንን ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ አቶ ኢብራሂም ተማም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የጤና ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል ።
ይህንን ተግባር ውጤታማ በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋ በመፍጠር በክልላችን ዘርፈ ብዙ ዕቅድን ለማሳካት ከፌደራል፣ ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያጣመረ ግብረ ኃይል ተቋቁመው በክልሉ በሚገኙ ስድስት ዞኖች ላይ የተቀናጀና ዘርፈ ብዙ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ የቢሮ ኃላፊው አንስተዋል ።
አክለውም ግብረሃይሉ ከዞንና ወረዳ መዋቅር ጋር በመቀናጀት በየደረጃው ተጨማሪ ግብረሃይል በማቋቋም የድጋፋዊ ክትትልና የግምገማ ስርዓትን በማጠናከር፣ የመረጃ ሰንሰለትን ቀልጣፋ በማድረግ ሰፊ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንዳሉ ነው ያወሱት ኃላፊው ።
የወባ በሽታ ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር እንዲያስችል ቋሚና ጊዜያዊ የመራቢያ ቦታዎች ማለትም ውሀ ያቆሩ ቦታዎችን ማፍሰስና መድፈን፣ አጎበርን ማሰራጨትና በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ የኬሚካል ርጭትና ታማሚዎችን የማከም ስራዎች በሰፊ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ኢብራሂም ጠቁመዋል ።
በዚህ መሠረት 284, 081 ጊዜያዊ እና 377, 044 ሜትር ስኩዌር ቋሚ የመራቢያ ቦታዎችን የመለየትና የማፍሰስ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
የአጎበር ስርጭቱን በሚመለከት ለ3 ዓመት የሚያገለግል በ2015 ዓ/ም በክልል ደረጃ 1,236,286 አጎበር የተሰራጨ ቢሆንም 60,158 አጎበር ተጠቃሚዎቹ በትክክል ሳይጠቀሙና ባልተገባ ቦታ ያስቀመጡት በዘመቻ ወቅት በክትትል ቡድን መገኘቱን ገልጸዋል ። በመሆኑም አጎበርን በትክክል እንዲጠቀሙ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርተዋል ተብለዋል ።
ከኬሚካል ርጭት አንጻርም በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ወባማ ተብሎ በተለዩ 8 ወረዳዎች 80,470 ቤቶች ርጭት እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
ከመከላከያ መንገዶች በተጨማሪ በማከም ስራ ላይም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ያለና በጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ደረጃ የመመርመርያ መሣራያና መድኃኒት ማሰራጨት መጀመሩን ገልጸው በክልሉ ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ጤና ኬላዎች የተጠናከረ አገልግሎትና የህክምና ስራ መጀመሩን አክሏል ።
ይህም ወባ በሽታን ከመከላከል ባለፈ በአጠቃላይ የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓቱን ከማነቃቃትም አልፎ ለአፈፃፀም ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት ።
የመድኃኒት አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተው ለዚህም ከፌደራል ጤና ሚ/ር ፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በዕቅድና በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ ኃላፊው አክሏል ።
በዚህ መሠረት በግንቦት እና ሰኔ ወር 301,360 የወባ ታማሚዎችን የሚያክም በክኒንና መርፌ መልክ መድኃኒት ቀርቦ እንደተሰራጨ ተገልጿል።
ከመድኃኒት ምጣኔ አንጻር ከዚህ በፊት በግምት ከሚቀርብበት አሰራር በመውጣት በዕቅድ እንደሚመራና በየሦስት ወር ዕቅዱ እየተከለሰ እንደሚቀርብና ይህም የአቅርቦት ችግሩን እየቀረፈ መምጣቱን ኃላፊው ጠቅሷል ።
በግብዓት አቅርቦት ስርጭት ላይ ክትትልና ቁጥጥር አንዱ የግብረሃይሉ ተግባር በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል ።
ይሁን እንጂ በዘርፉ ላይ ኮንትሮባንድ መበራከት የህክምና ተግባሩንና የመድኃኒት ፈዋሽነቱን በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬ ውስጥ ከመክተቱም በላይ በተቋሙ ውስጥ በሚገኙ የስነ ምግባር ብልሽት ባላቸው ባለሙያዎች ወደ ውጭ በማውጣት በመንግስት ጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት እንደሌለ ተደርጎ በህዝብና በመንግሥት መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑንም አልሸሸጉም ።
በመሆኑም ከመንግሥት ህክምና ተቋማት በህገወጥ መንገድ መድኃኒት ባወጡት ባለሙያዎች ላይ እና ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠና ደረጃውን ያልጠበቁ መድኃኒት በሚያዘዋውሩና በሚሸጡ የግል ህክምና ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ህጋዊ ርምጃ ከመውሰድም በላይ በቁጥጥር ስር ውለው በፍርድ ቤት ክስ ሂደት ላይ ያሉት እንዳሉ ጨምረው ገልጸዋል ።
ከውጤት አንጻርም ሲገመገም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቅንጅት መሻሻል ፣ የክትትልና ድጋፍ፣ የግምገማና ሪፖርት ስርዓት መጠናከር፣ ወደ ጤና ተቋም መጥቶ የሚመረመር ሰው ቁጥር መጨመር፣ ሞትና ፅኑ ህሙማን መቀነስ፣ ከአገልግሎት አንጻር ከመዘናጋት በመውጣት ባለሙያዎች ወደ ስራ መግባትና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እየታየ መምጣቱን አቶ ኢብራሂም ጨምሮ ገልጸዋል ።
የቢሮ ኃላፊው የበሽታው አስከፊነት የማስገንዘብ ስራ በመሰራቱ የሐይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች ፣ የሚዲያ አካላትና ህዝቡ ዘንድ ባለቤትነት ስሜት መፍጠር መቻሉን አንስተው ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል ።
የቢሮ ኃላፊው አክለው የወባ በሽታ በክልሉ በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ከማስከተሉም በላይ የሰው ልጅ የመኖር መብቱንና ተስፋውን ጥያቄ ውስጥ እያስገባ መሆኑን በማንሳት ፤
በሽታውን ከመከላከል አልፎ እስከ መቆጣጠር በዕቅድ መመራት ፣በየደረጃ የሚገኝ የአመራርና ባለሙያዎች ቅንጅት ፣ የመንግስትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ርብርብ፣ ህገወጥ ተግባራትን ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የህዝብ ባለቤትነትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል ።
የወባ በሽታ ወረርሽኝ በመከላከልና መቆጣጠር ረገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ከቤተሰብ፣ መንደር እስከ ቀበሌ ድረስ አከባቢውን ንጹህ በማድግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት ልሰራ ይገባል የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት ነው።
