
ሀገራዊ ምክክሩ በውይይት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር፤ ኢትዮጵያ በምክክር ችግሮቿን ለመፍታት የነበሯት በርካታ ዕድሎችና አጋጣሚዎች አምልጠዋት እስካሁን መዝለቋን አስታውሰዋል።
በተለያዩ ዘመነ-መንግሥታት ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ሰፊ ዕድል የነበራት ቢሆንም ወደ ተግባር መቀየር ተስኗት መቅረቱንም ይናገራሉ።
ለአብነትም በኢህአዴግ ዘመን በምሁራን፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ጭምር የምክክር ሃሳብ ተነስቶ የነበረ መሆኑን አብራርተዋል።
በወቅቱ ኢትዮጵያ ምክክር እንደሚያስፈልጋት ቢታመንም ጥያቄዎችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ግን ተግባራዊ ምላሽ አለመገኘቱን ገልፀዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ ኢትዮጵያ መክራ ችግሮቿን በመፍታት በዋና ዋና ጉዳዮችም ላይ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚቻል ጽኑ እምነት ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አምባሳደር መሐሙድ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት ለምክክሩ ጉልህ ሥፍራ በመስጠት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረጉ የዘመናትን የሕዝብ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ገልፀዋል።
ለምክክሩ ሂደት መሳካት መንግሥት በቁርጠኝነት ድጋፍና እገዛ በማድረጉ ጭምር ምክክሩ እስካሁን በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በውይይት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።
የምክክር ሂደቱ ከአፈ-ሙዝ ትግል በመውጣት በሰለጠነ አግባብ የውይይት ባህልን በማዳበር ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ እልባት ማምጣት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የምክክሩ ሂደት የቅድመ-ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የምክክርና የክትትል ምዕራፎች ያሉት መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የምክክር ምዕራፍ ላይ ይገኛልም ብለዋል።
በመሆኑም በአዲስ አበባ የተጠናቀቀው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በቀጣይ በክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይንም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው አካል ሆኖ በ2014 ዓ.ም በአዋጅ መቋቋሙ ይታወሳል።
ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የፖለቲካ ባህልን ለማዳበርና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁነኛ መሠረት የሚያኖር መሆኑ ታምኖበታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
