የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ

Spread the love

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋምና ጥቅማቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሥምምነት አደረገ።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ሥምምነት አድርጓል።

በተጨማሪም ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ እንዲሁም ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ጋርም ሚኒስቴሩ ሥምምነቱን አድርጓል።

የመግባቢያ ሥምምነቱ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትሮችና የየተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ፈርመውታል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዜጎች በደላሎችና በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪ ቡድኖች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከአገር ይወጣሉ።

በዚህም በድንበር ጠባቂዎች፣ ታጣቂዎችና በተደራጁ ቡድኖች እጅ በመውደቅ ለከፍተኛ የጤና፣ የሥነ-ልቦና እንዲሁ የአካል ጉዳት፣ ወሲባዊ ጥቃት ብሎም ለሞት ይጋለጣሉ ብለዋል።

መንግሥት ባለው ዜጋ ተኮር ፖሊሲ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ አገራት ሄደው ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ወደ አገር የመመለስ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

እነዚህን ከስደት የተመለሱ ዜጎች መልሶ ለማቋቋምና ጥቅማቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ማድረጉን ጠቁመዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ምኞት ደራራ በበኩላቸው፤ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ላይ የሚሰሩ ሥራዎች በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን ለማከናወን ይረዳል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *