



በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በተገባደደው 2016 በጀት ዓመት ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ የተሰጠዉን ሀላፊነት ለመወጣት በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ከአቻ ክልሎች እንዲሁም ከተወካዮች ም/ቤትና ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋርም ተግባራትን በቅንጅት ማከናወን መቻሉን አፈጉባኤው ተናግረዋል።
በ6ኛ ዙር 3ኛ የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ በም/ቤቱ በተቀመጡ አቅጫጫዎች ላይም በትኩረት ለመስራት ጥረት መደረጉንም አፈጉባኤ ወንድሙ ኩርታ ተናግረዋል ፡፡
በዚህም አንዳንድ የአስፈጻሚ ተቋማት ከክልሉ ም/ቤት ጋር በቅንጅት ለመስራት ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ ነበርም ብለዋል፡፡
በሕገ-መንግስቱ በተቀመጠው ስልጣን መሠረት ምክር ቤቱ ጉባኤዎችን ማካሄድ፣ የአስፈፃሚ ተቋማትን የዕቅድ አፈፃፀም መገምገም፣ ግብረ-መልስ የመስጠት፤የመስክ ምልከታ ማድረግ፤ የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ መድረኮችን በመፍጠር ሲሰራ መቆየቱንም ጨምረው ገልጸዋል ።
በክልሉ በሚዘጋጁ ረቂቅ አዋጆች ላይ ግብዓት በማሰባሰብ፣ የም/ቤቶችን የጋራ ምክክር ፎረም በማካሄድና ለቀጣይ የተሻለ አሰራር ለመዘርጋት በአመራሩና በባለሙያዎች የልምድ ልዉዉጦች መደረጋቸውንም አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ም/ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤው ለተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑን በመጠቆም በሚቀርቡ የም/ቤቱ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ዉይይትና ምክክር በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የክልሉን ህዝብ ዉክልና በአግባቡ በመወጣት ህገ መንግስታዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡም አፈጉባኤ ወንድሙ ኩርታ አሳስበዋል።
በታጠቅ አበበ
