በ2016 በጀት ዓመት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋግጡ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል። ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

Spread the love

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ከምክርቤቱ አባላት ለተነሱላቸው አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክርቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበና ጉባኤ በሁለተኛው ቀን ውሎ በተነሱ የአስፈጻሚ ተቋማት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ከምክርቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በግብርና ልማት ስራዎች ፣በንጹህ መጠጥ ውሃና መስኖ ተቋማት ግንባታ፣በሌማት ትሩፋት ስራዎችና በቡና ልማት ስራዎች ላይ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል ፡፡

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች የታዩበት መሆኑንና ከዚህም ጋር ተያይዞ የአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ገንዘቦች ወደ አካውንት ከማስገባት አንጻር ያሉ መሰረታዊ ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚገባ በምላሻቸው አስታውዋል ፡፡

በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ወደ አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ መቻሉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ ይሰራበታል ብለዋል ፡፡

በገቢ አሰባበሰብ፣በስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎችና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች የሚያበረታታ ስራዎች ተከናውነዋልም ብለዋል ፡፡

በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭት በህብረተሰቡ ላይ አሁንም ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ቀጥሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ችግሩን ለመቅረፍ ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ከመድሀኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን የማስፋት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ ህብረተሰቡ በዚህ በመሳተፍ ህክምና ወጪውን በመቀነስ ጤናውን እንዲንከባከብ ምክርቤት አባላት ድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል ፡፡

በክልሉ የተጀመረውን የብሔረሰቦችን ባህል ፣ቋንቋ፣ታሪክና ወግ ለማልማት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከቋንቋ ተናጋሪ ብሐረሰቡ ተወላጆች ጋር በቀራረብ አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ ይሰራልም ብለዋል ፡፡

በክልሉ ብሔራዊ ፓርኮች ለምተው እንደሚገኙ ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ አዳዲስ ፓርኮችን ከልሎ ለማልማት ሰፊ ጥናት የሚፈልግ በመሆኑ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየትና በመግባባት በጥንቃቄ በጥናት ላይ የተመረኮዘ ምላሽ መስጠት ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

በመንገድና ድልድይ መሰረተ ልማቶች የማስፈጸም አቅም እየጎለበተ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የህብረተሰቡን ፍላጎት የተሟላ ለማድረግ የተጀመረውን የህብረተሰብ ተሳትፎ አጠናክረነረ እናስቀጥላለን ብለዋል ፡፡

በመደመር ትውልድ በተገኘ ሀብት በክልሉ 6 ቤተ መጻህትን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በዘንድሮ ዓመት በቦንጋ ከተማ መጀመሩና ይህም በሂደት በሌሎቹ ተጠናክሮ እንደሚሰራም አብራርተዋል ፡፡

በከተሞች የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል በተደረገው ስራ መሻሻሎች መኖራቸውን በማመላከት ህገ ወጥነትን ለመከላከል የሚሰራው ስራ ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል ፡፡

ግንባታቸው የተጓተቱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት እንደየችግራቸው ስፋት እየታየ ምላሽ የመስጠት ሂደቱ ተጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉ አብራርተዋል ፡፡

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የፍትሐዊነት ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻር የክልሉ መንግስት ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ እና የኔት ወርክ አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማስፋት የክል መንግስት በትኩረት ይሰረበታል ብለዋል ፡፡

በክልሉ ተረጂነትን ለማስቀረት የሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል እንዲያስችል በዞኖች ተጠባባበቂ ምርት ለማዘጋጀት የመሬት ዝግጅቶችን በማመቻቸት ከባለሀብቱ ጋር በመቀናጀት በቂ ምርት ለማምረትና ራስን ለመርዳት በራስ አቅምን የማጎልበት ስራ ከዞኖች ጋር እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል ፡፡

ርዕሰ መስዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ከምክርቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት የክልሉ አስፈጻሚ ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም በምክርቤት አባላት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል ፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *