








የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የዳሎል ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ 502ኛ ህዳሴ ኮር የመከላከያ ሰራዊት መኖሪያ ካምፕ መርቀው ከፍተዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለፁት የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን የሀገርን ዳር ድምበር በማስከበር ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈፅመዋል ብለዋል።
ክልሉ ከተደራጀ ጊዜ አንስቶ የክልሉ ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች በመከናወናቸው ሰላም ማረጋገጥ እንደተቻለ ገልፀዋል።
የክልሉ ማህበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይትም በክልሉ አንድ አንድ አከባቢዎች የተፈጠረውን አለመረጋጋት በህዝባችን እና በሰራዊቱ ጥረት ሙሉ ሰላም ተረጋግጧል ብለዋል።
የሰራዊቱ ካምፕ በአካባቢ ላይ መኖሩ ከዚህ ቀደም በድንበር አከባቢ ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን ገልፀው ለአከባቢው ሰላም መረጋገጥ ባለፈ ለክልላችን ብሎም ለአጎራባች ዞኖች ፀጥታ ስጋት እንዳይፈጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት 502ኛ ህዳሴ ዕዝን የሰራዊት ማረፊያ ካምፕ ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በክልሉ ሰላም መረጋገጥ እየከፈለ ላለው መስዕዋትነትም አመስግነዋል።
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ በበኩላቸው የህዳሴ ኮር ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
ሰራዊቱ የተሰጠውን ሀገራዊ ግዳጅ በተሳካ ሁኔታ እየተወጣ መሆኑን ተናግረው የ502ኛ ህዳሴ ኮር አመራሮችና አባላቶች በአከባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሀገራችን በተለያዩ ጊዚያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ግንባር ቀደም በመሆን መስዋዕትነት እየከፈለ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊታችን ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብራክ የወጣ ለሕዝብ ደኅንነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የአካልና የህይወት መስዋእትነት የሚከፍል ብሔራዊ ኃይል መሆኑን ጠቁመዋል።
ከራሱ አልፎ በሌሎች አገሮች ውስጥ በህዝባዊ ወገንተኝነት ባህሪው ሰላምና መረጋጋትን ተልዕኮዎች ላይ በመሳተፍ አኩሪ ግዳጅ የፈፀመና በመፈፀም ላይ የሚገኝም ነውም ብለዋል።
በዞኑ አንድ አንድ አከባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር ተቀይሮ ወደ ሰላም ብቻ ሳይሆን ወደ ዘላቂ ልማት መንገድ ላይ ለመሆናችን ህዝቡ ፤ መከላከያ ሰራዊታችን ፣ የፌደራል ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች በጋራ በከፈሉት ዘርፈ ብዙ መስዋዕትነት መሆኑ ተናገረዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የሬጅመንት መኖሪያ ካምፕ ለመገንባት 17 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ወጪ ሆኖ መገንባት መቻሉ ተገልጿል።
502ኛ ህዳሴ ኮር የመከላከያ ሰራዊት መኖሪያ ካምፕ ለማደራጀት ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትም የምስጋና ሰርተፍኬት እንደተበረከተላቸው የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ።
በምረቃው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ የዕዝ ኮማንድ ጄነራል መኮንኖች የኮር አዛዦች የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ካምፑን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
