በዘንድሮው የመኸር እርሻ እስካሁን 7 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር ተሸፍኗል – ግብርና ሚኒስቴር

Spread the love

በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 7 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር መሸፈኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘር ከተሸፈነው ውስጥ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የለማ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ላቀው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር ወቅት 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

ለማልማት ከታቀደው ውስጥ በባህላዊና በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

ከታረሰው መሬት ውስጥ 7 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

ለማልማት ከታቀደው መሬት 616 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አያይዘው ገልጸዋል።

ለዚህም ከግብዓት አቅርቦት፣ ለአርሶና ለአርብቶ አደሮች ስልጠና እንዲሁም የልማት ጣቢያ ሰራተኞችን በማሰልጠን ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

በዘር ከተሸፈነው ውስጥ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የለማ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

በዘር ከተሸፈኑ ሰብሎች መካከል ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ገብስን የመሳሰሉ ሰብሎች ተጠቃሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የግብዓት አቅርቦት ላይም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ከበደ ለዚህም የማዳበሪያ አቅርቦት፣ ጸረ-አረም ኬሚካል እንዲሁም ሜካናይዜሽን ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን መልክተዋል።

ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች ቅንጅታዊ አስራርን በመተግበር እንዲፈቱ መደረጉን አስታውሰው በ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

እስካሁን ተገዝቶ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 15 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉንም አስረድተዋል።

ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘም የግልና የመንግሥት ምርጥ ዘር አባዥ ድርጅቶች ምርጥ ዘር እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረቶች መኖራቸው መለየቱን የተናገሩት አቶ ከበደ ችግሩን ለመፍታት ክልሎች በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ እንዲደጋገፉ የሚያስችል አቅጣጫ በግብርና ሚኒስቴር መቀመጡን አመልክተዋል።

በምርት ዘመኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ላይም ውጤታማ እንቅስቃሴ መደረጉን አስታውሰው በ2016/17 የምርት ዘመን 107 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት መገኘቱን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *