እናቶችንና አቅመ ደካሞችን መርዳትና ማገዝ ሀገርን መርዳትና ማገዝ ነው ፦ ክቡር አቶ ጸጋዬ ማሞ

Spread the love

በአቶ ፀጋ ማሞ አስተባባሪነት በጉራፈርዳ ወረዳ ኦቱዋ ሴጋ ቀበሌ ነዋሪ ለሆኑ አቅመ ደካማ እናት የቤት መስሪያ ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ በሚዛን አማን ከተማ የሚገኙ ወጣቶችን በማስተባበር በጉራፈርዳ ወረዳ ሴጋ ቀበሌ ለሚገኙ አቅመ ደካማ እናት 24 ቆርቆሮ ፣ ምስማር ፣ ፍራሽ ፣ ብርድ ልብስና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገዋል።

አቶ ጸጋዬ ድጋፉን ካስረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር እናቶችና አቅመ ደካሞችን መርዳት ሀገርን መርዳት ነው ብለን ድጋፉን ይዘን መጥተናል ብለዋል። የቀበሌው ወጣቶች ለአቅመ ደካማዋ ያደረጉትን የሳር ቤት እድሳት በማህበራዊ ሚዲያ ማየታቸውን የገለፁት ኃላፊው የወጣቶቹ ድጋፍና የአቅመ ደካማዋ እናት ምስጋና ስሜት የሚነካ በመሆኑ በሚዛን አማን ከተማ የሚገኙ ወጣቶችን ማስተባበራቸውን ገልፀዋል።

በዚህም በሁለት ቀናት ውስጥ 24 ቆርቆሮ ፣ ሚስማር ፣ ፍራሽ ፣ ብርድ ልብስና ከ20ሺ ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸው ጥሪ ያደረጉላቸው ወጣቶች ለሰጧቸው ፈጣን ምላሽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቤቱ ተሰርቶ እስከሚጠናቀቅ ድጋፍና ክትትሉ ይቀጥላል ያሉት ኃላፊው ስንተባበር የማንሻገረው ችግርና የማንወጣው ነገር አይኖርም ብለዋል።

ይህም ተግባር ለሰብዓዊነት ሲባል የተፈጸመ ነው ያሉት አቶ ጸጋዬ ይህን ክረምት በሁሉም አካባቢዎች አቅመ ደካሞችና አረጋዊያንን በማገዝ ልናሳልፍ ይገባል ብለዋል። አቅመ ደካማዋ እናት በህይወት እስካሉ ድረስ በየወሩ አንድ ሺ ብር ድጋፍ ለማድረግም ኃላፊው ቃል ገብተዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ኬና በበኩላቸው በጎነት የሀገራችን መገለጫ መሆኑን ገልፀው በተለይም በግለሰብ ደረጃ እንደዚህ አይነት ተግባራት መደረጉ መነቃቃት ፈጥሮብናል ብለዋል።

አቶ ፀጋዬ ማሞ በራስ ተነሳሽነት ያደረጉት ተግባር ለሌሎችም መነቃቃት ፈጥሯል ብለው ለተደረገው ድጋፍ በዞኑ ስም አመስግነዋል።

በቀጣይም ተባብረን እንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ ያሉ እናቶችን የመታደግ ስራ እንሰራለን ያሉት አቶ ዮናስ ለወይዘሮ ፋኒ ጋዝያብ የሚደረገውን ተግባር በማጠናከር የበኩላችንም እንወጣለን ብለዋል።

ወይዘሮ ፋኒ ጋዚያብ ለተደረጋቸው ድጋፍ አመስግነው ልጆቻቸው በህይወት ባለመኖራቸው ብቻቸውን በችግር ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ዝናብ ቤታቸውን ሊያፈርስ በተጠጋበት በዚህ ሰዓት በተደረገላቸው ድጋፍ ከልብ አመስግነዋል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *