በአከባቢው ያለውን የደን ሀብት በተገቢው መንከባከብና መጠበቅ ይገባል፦ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ

Spread the love

የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር አመራሮች እና ባለሙያዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን በመገኘት ሁለተኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ መርሀ ግብር አከናውነዋል።

በክልሉ ካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ምቺት ቀበሌ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ላይ ሚኒስትር ደኤታዎችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን ያለው የደን ሀብት እጅግ የሚያስደንቅ ነው ብለዋል።

ይህን የደን ሀብት በተገቢው ከመንከባከብና ከመጠበቅ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያላቸውን ችግኞች መትከልና መንከባከብ እንደሚገባ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ተናግረዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ደን እየጠበቀ ከደን የሚያገኘውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የማሳደግ ተግባር መከናወን እንዳለበትም አመላክተዋል።

ማኒስትር ዴኤታው ዛሬ በክልሉ የሚደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ አምና የተተከሉ ችግኞች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታን ለመየት ያለመ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው ሀገራችን የጀመረችውን የአርንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እውን ለማድረግ በክልሉ እስከአሁን ከ646 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአርንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር መተከላቸውን ጠቅሰዋል።

የአከባቢው ማህበረሰብ ከደን ጋር አብሮ የሚኖር መሆኑን ጠቅሰው በአከባቢው የሚገኘው የተፈጥሮ የደን ሀብት ከዚህ ቀደም ከነበረው እየሳሳ መምጣቱን አንስተው ይህንን ችግር ለመቅረፍ በየአመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና በሌሎች ፕሮግራሞች የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች መትከል መቻሉን ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአምና ጀምሮ በክልሉ እያደረገ ላለው ድጋፍም አቶ ማስረሻ በክልሉ መንግሥት ስም አመስግነዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳር አቶ እንደሻው ከበደ በበኩላቸው የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴር በዞኑ በአርንጓዴ አሻራ እና በክረምት በጎ ስራ ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረው ሚኒስተዠቴር መስሪያቤቱ የጀመረውን ድጋፍና መልካም ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

አቶ እንዳሻው አክለውም በዞኑ በዘንድሮ የክረምት በጎ ስራ በ14 የስራ ዘርፎች ከ222 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ከፍሎችን በማሰተፍ እየተሰራ እንዳለ ጠቁመዋል።

የጊምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ጥላሁን እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ባሉበት ወቅት የግብርና ሚኒስቴር በወረዳው የአረንጓዴ አሻራ ከማሳረፍ ባለፈ ለአጋማ ትምህርት ቤት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የግብርና ሚኒስቴር አመራሮች እና ባለሙያዎች በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ ከችግኝ ተከላ ባለፈ የሌማት ትሩፋት ስራዎች ጉብኝት፣ በጊምቦ ወረዳ ምቺት ቀበሌ በአጋማ ትምህርት ቤት ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ አና የአረጋዊያን ቤቶች ግንባታ ሥራ ያለበት ሁኔታ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *