የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በወቅታዊ የገቢ አሰባሰብ ሂደትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በክልሉ ከመነሻው ጀምሮ ሁሉን ባሳተፈ ሁኔታ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው አስፈላጊውን መድረክ በመፍጠር በሁሉም ዞኖች የደረጃ “ሐ” የዕለት ገቢ ግመታ ስራ እና የአሰባሰብ ስራዉ በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች በየሶስት ዓመቱ መገመት የነበረበት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የዕለት ገቢ ግመታ ለስድስት ዓመት ሳይገመት እንደቆየ አስታውሰው ባለድርሻ አካላት እና ግብር ከፋዮን በተገቢው መንገድ በማሳተፍ ተግባሩ ተከናዉኗል።
በግመታው ሂደት ከግብር ከፋዩ የቀረበዉ ቅሬታ ከሚጠበቀው በታች ነው ያሉት ኃላፊዋ የቀረቡትም ቅሬታዎች በተገቢው መንገድ በተቀመጠው ህጋዊ አሰራር ታይቶ ምላሽ ተሰቷል ብለዋል።
በክልሉ ከ57 ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የገለጹት ወ/ሮ ህይወት አሰግድ እስከ ነሐሴ2/2015 ድረስ 40 ሺህ 628 ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ ከፍለዋል ብለዋል በዚህም 229 ሚሊዮን 179 ሺህ 294 ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ይህም የዕቅዱን 63% በላይ እንደሆነ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ አስረድተው የተሰበሰበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ እንዳለውም ገልፀዋል።
ወ/ሮ ህይወት አሰግድ አምና በዚህ ወቅት ከ45 ሺህ ግብር ከፋዮች 142 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውሰው በንጽጽር ዘንድሮ የተሻለ አፈፃፀም እንዳለው ገልፀው ግብራቸውን በታክስ አስተዳደር አዋጁ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ በታማኝነት ለክልላቸው ልማት የከፈሉትን ግብር ከፋዮች አመስግነዋል።
በተለያዬ ምክኒያት በወቅቱ ግብራቸውን ያልከፈሉ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ወለድና አስተዳደራዊ ቅጣት ሳይበዛባቸው ግብራቸውን ሳይዘገዩ እንዲከፍሉ ያሳሰቡት ኃላፊዋ ከነሐሴ 1/2015 _ ጥቅምት 30/2016 ዓ/ም የደረጃ ለናሀ ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ወቅት በመሆኑ በወቅቱ ግብራቸውን እንዲከፍሉም ጥሪ አቅርበዋል ።
