አካል ጉዳተኞች በዘንድሮ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ለመሳተፍ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል- ፌዴሬሽኑ

Spread the love

አካል ጉዳተኞች በዘንድሮ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ለመሳተፍ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

በዚህ ዓመት በመላው ሀገሪቱ ለስድስተኛ ጊዜ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

የዘንድሮው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ነገ እንደሚካሄድና በዚህም 600 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።

በመርኃ ግብሩ ከልጅ እስከ አዋቂ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኝ በመትከል ለነገ ሀገር ተረካቢዎች የምትመች ሀገር ለማስረከብ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሃላፊነታችንን እንወጣ ማለታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፌዴሬሽኑ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።

ፌዴሬሽኑ አባላቱን በማስተባበር በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ነገ በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለመሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ስራቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዕለቱ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተዘጋጀው ቦታ የችግኝ ተከላው እንደሚከናወንና በመርሃ ግብሩ 17 ሺህ አካል ጉዳተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

ችግኝ ከመትከል በተጨማሪ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የእንክብካቤ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲያኖሩም አቶ አባይነህ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *