በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦችን የጋራ ዕሴት ማጎልበት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ሲል የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ገለፀ

Spread the love


የብሔረሰቦች ምክር ቤት የክልሉን ህገ መንግስት የመተርጎም፣ አጣሪ ጉባኤ የማደራጀት እንዲሁም በክልሉ ዉስጥ የሚነሱ ችግሮችን መፍትሔ የማፈላለግ እና የህዝቦችን ባህልና ታሪክ የማጠናከር ስልጣን አለው፡፡


በክልሉ ከሚገኙ ከ13 ነባር ብሔር/ብሔረሰቦች የተወከሉ 70 አባላትን ያቀፈዉ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት እያንዳንዱ ብሔር/ብሔረሰብ አምስት ተወካዮች ሲኖሩት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባለበት ተጨማሪ አምስት ተወካዮች የሚኖሩት በመሆኑ በዚህም መሠረት የካፋ ዞን 20 (ካፈቾ 10፣ ናኦ 5ና ጫራ 5)፣ ዳዉሮ ዞን 5፣ ቤንች ሸኮ 8 (3 ሸኮና 5 ቤንች)፣ በኮንታ 5፣ በሸካ ዞን 12 (ሸካቾ 5፣ ማዣንግ 5ና ሸኮ 2) እንዲሁም በምዕራብ ኦሞ ዞን 20 የብሔረሰቦች ምክር ቤት ተወካዮች አሉ።
የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ የምክር ቤቱን የሁለት ዓመታት የሥራ ጉዞ አስመልክተው እንደገለፁት የብሔረሰቦች ምክር ቤት በህገ መንግስት በተሰጠው ስልጣን መሠረት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ምክር ቤቱ የክልሉን ህዝቦች አብሮነት፣ አንድነትና ትስስርን ለማጠናከር እንዲሁም የዜጎችን ፖለቲካዊ ተሳተፎ ለማሰደግ እየሠራ ያለ መሆኑን ገልጸው የብሔር/ብሔረሰቦችን የጋራ ዕሴቶች ለማጎልበት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ከተቋቋመ በኀላ ብዝሃነትን መሠረት አድርጎ የክልሉን ብሄረሰቦች ምክር ቤት መቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ በክልሉ ህገ መንግስት በአንቀፅ 65 መሠረት እራሱን የቻለ ምክር ቤት መቋቋሚያ አዋጅ 10/2014 ወጥቶለት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ተቋቁሞ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችንና የራሱን ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደስራ የገባ መሆኑን አቶ መቱ አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከነባሩ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ልምድና የአሰራር መመሪያዎችን በመውሰድ ከዚህ በፊት በነባሩ ክልል ተለይተው የሚፈቱ እና በአዲሱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚፋቱ ችግሮችን የመለየት ስራ በሰፊው መስራቱን አፈጉባኤው ተናግረዋል፡፡
የብሔረሰቦች ምክር ቤት የአባላት የአሰራር ስነ ስርዓት ደንብ 1/2016 በማውጣት እና በማጽደቅ ለምክር ቤቱ አባላት በደንቡ ላይ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ስልጠና መሰጠቱን የተናገሩት አቶ መቱ በምክር ቤቱ ውስጥ ዳይረክቶሬቶችና በቂ የሰው ሃይል በተገቢው እንዲዋቀር የማድረጉ ተግባር በሂዳት ላይ ያለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህንን የሰው ሃይል ማሟላት የተቋሙን ስዕል የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት አቶ መቱ አኩ ለዚህም የሚመጥን ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የምክር ቤቱ የቀጣይ አቅጣጫ እንደሆነም አብራርተዋል
የክልሉን ብሔር/ብሔረሰቦች መብት ማስከበርና በህገ-መንግስት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር በክልሉ ያሉ ነባር ብሔረሰቦች ትክክለኛ መጠሪያቸውን በተገቢው መንገድ እንዲታወቅ የማድረግ ስራ መሰራቱን የጠቆሙት አፈጉባኤው በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የክልሉን ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋና ወግ ለማሳደግ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በክልሉ የብሔር/ብሔረሰቦችን አንድነት፣ ሰላምና ባህላዊ ዕሴቶችን ሊያጎለብቱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ስራዎችን ለመስራት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ያስረዱት አቶ መቱ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት የበጀት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና የህግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴን ለማደራጀት በምክር ቤቱ የአሰራር እና የአባላት ደንብ አንቀፅ 62/3 ላይ በተቀመጠው መሠረት በመመልመል ለእያንዳንዱ ሰባት አባላት ተመርጠው ቋሚ ኮሚቴዎችን የማደራጀት ተግባር መከናወኑን መቻሉን አንስተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ቋሚ ኮሚቴ እና ሌሎች የሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎችን በማምጣት በታችኛው የዞን መዋቅር ላይ በበጀት ቀመር ዝግጅት፣ አጠቃቀምና መረጃ አያያዝ ስርዓት ዙሪያ ስልጠና የሰጠ መሆኑንም አፈጉባኤው ገልፀዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ብሔረሰቦች እኩልና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ቀጣይነት ባለዉ መልኩ በትኩረት እንደሚሠራ ያነሱት ዋና አፈ ጉባኤ ለዚህም አጋዥ በሆነዉ የበጀት ቀመር ዙሪያ የተለያዩ የዘርፉ ምሁራንን በማሳተፍ እየሰራ እንዳለ ተናግረዋል።
በክልሉ አሁንም በልማት፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ተጠቃሚ ያልሆኑ አካባቢዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ መቱ ለእነዚህ አካባቢዎች ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ስለሚያስፈልጋቸው ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ለማከናወን የታቀዱ ተግባራት እንዳሉም አንስተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ የተሰጠዉን ተልዕኮ ለመወጣት ያስችለዉ ዘንድ ጉቤዎችን በየወቅቱ እያካሄደ ይገኛል ያሉት አፈ-ጉባኤዉ በክልሉ የብሔረሰቦችን አንድነትንና የጋራ ዕሴቶችን ለማጠናከር ጥናቶችን የማካሄድና መሰል ተግባራት እየተከናወኑ እንዳሉና በብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ ያለውን ነባር ዕሴቶችን ለህዝቡ እኩል ተደራሽ እንዲሆኑ በሸካቾ፣ በማዣንግ እና በሸኮ ብሔረሰቦች የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውንና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከክልሉ ጋር በሚዋሰኑ አጎራባች ክልሎችና ከጎረበት ሀገር ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አከባቢዎች ጋርም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርና በአርብቶ አደሩ አከባቢ አልፎ አልፎ የሚታየዉን ግጭት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ መቱ የብሔረሰቦችን ባህልና ዕሴቶችን የማስጠናቱ ተግባር እና በሀገረ-መንግስት እና በሰላም ግንባታ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባህላዊ የዳኝነትና የእርቅ ስርዓቶች ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ናቸው ያሉት አፈጉባኤ አቶ መቱ በሰላም ዕሴት ግንባታ እና በፌደራሊዝም ስርዓት ላይ ለምክር ቤቱ አባላት ግንዛቤ ለመፍጠር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ብሔር/ብሔረሰቦች የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሀሳብና ህገ መንግስታዊ ግንዛቤ እንዲኖረቸው ለሶስት ተከታታይ ወራት በክልሉ ባሉ ኤፍ ኤም ጣቢያዎች በሰባት ቋንቋዎች የሚዲያ አስተምሮ ስራ መሰራቱን ያነሱት አቶ መቱ በቀጣይ በክልሉ ባሉ አራት ኤፍ ኤሞች በሁሉም ቋንቋ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰራ ነው ብለዋል።
በየአከባቢው የሚታዩ ግጭቶችን በጋራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በሠላም አብሮ ለመኖር የሚያግዙ መድረኮች በመፍጠር ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይም በ2017 በጀት ዓመት በሰፊው ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን የተናገሩት አፈጉባኤው ለዚህም ሁሉም የባለድርሻ አካላት የድርሻቸዉን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በተከተል ወ/ ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *