የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የተፈጥሮ ፀጋዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን የሸካ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ

Spread the love

በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብቶችና አስደናቂ ስፍራዎች በስፋት ሊጎበኙ የሚችሉ ናቸው፡፡


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም በርካታ የቱሪዝም መስህቦችን አካልሎ የያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እነዚህ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ለጉብኝት በሚያመች መልኩ ማልማት ተገቢ ነው ፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች ውስጥ የሸካ ዞን አንዱ ሲሆን በዞኑ ከ135 በላይ የሚሆኑ ስፍራዎች በተፈጥሮ መስህብነት የተመዘገቡ ሲሆኑ ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የሚፈሱ ወንዞች፣ እጅግ ውብ እና ማራኪ ፏፏቴዎች፣ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች እና የዱር አራዊት ይገኙበታል፡፡
ከ2 ሺህ 6 መቶ 72 ሜትር ከፍታ በላይ በተራሮችና በቀርከሃ ተከቦ የሚገኘው የጋንዲዮች ሀይቅ፣ ተዓምራዊ የሸክሸኮ ፏፏቴና ጥቅጥቅ ደን ተፈጥሮ ምን ያህል ለሸካ ዞን እንዳደለች ካሉት ማሣያዎች ጥቅቶቹ ናቸው፡፡
የሸካ ዞንን የቱሪዝም አቅሞችን ለማሳደግ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተግባሩ እንዳሻው አንድ የደጋ ሀይቅ፣ 41 ፏፏቴዎች፣ 11 ኩሬዎችና በዩነስኮ የተመዘገበ የሸካ ደን በባዮስፌር በዞኑ ከሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች መካከል የሚገኙ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
እነዚንና ሌሎችን ያልለሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፀጋዎችን የማልማት፣የመጠበቅና የመንከባከብ ስራዎች ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ አካላት በዕቅድ ይዘው ጅምር ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው ከዞኑ መንግሥት በጀት ተይዞ ሀገርን እንወቅ ክበብ ከዞን ጀምሮ እስከ ተቋማት ድረስ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የማስተዋወቅ ስራ በሰፊው እየተሰራ እንዳለ ታዋቂ የሚዲያ ባለሙያዎችንና ሌሎች አካላትን ወደ ዞኑ በመጋበዝ የማስተዋወቅ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን የመለየት፣ በሀገር ውስጥና ለሌሎችም የማስተዋወቅ ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ የሚሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተግባሩ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ብዙም ከዞን ማዕከል የማይርቁ መሆናቸውን ጠቅሰው የሸክሸኮ ፏፏቴና ዋሻ፣ የጋንዲዎች ሀይቅ፣ ጋሀማሆ ፏፏቴ፣ አጫ ፏፏቴ፣ ዱሻ ዋሻ እና የጋማድሮ ፏፏቴ ጉብኝት ማድረግ የሚቻልባቸው ከዞኑ ከቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ጥቂቶቹ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ እንደ ሸካ ዞን ሶስት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በዕቅድ ደረጃ መያዙን ያነሱት አቶ ተግባሩ የጋንዲዎች ሀይቅ መንገድን በጠጠር የማልበስ ስራ በጀት መያዙን፤ በማሻ ወረዳ የሸክሸኮ ፏፏቴና ጋማሆ ፏፏቴ በባለሀብቱና በዞን መንግሥት በጀት ዕቅድ እንዲሰራ የ2017 በጀት ዓመት የመምሪያው የዕቅድ አንዱ አካል የተደረገ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
በዞኑ ቱሪዝም ዘርፍ የሚታዩ ውስንነቶችን በመቅረፍ በቀጣይ የቱሪዝም አቅሙ የበለጠ ጎልቶ እንዲወጣ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት አቶ ተግባሩ የክልሉ ባህል፣ ቱርዝምና ስፖርት ቢሮ ከኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚንስቴር ጋር በመቀናጀት በቅርቡ ወደ ሸካ ዞን በመምጣት ያሉትን የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በጂኦ ስፓሻል የመለየት ስራ መስራቱን ገልፀው የመስህብ ቦታ የመመዝቡ ስራ መጠናቀቁን ነው የተናገሩት፡፡
በባህልና በቋንቋ ዘርፍ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል ያሉት አቶ ተግባሩ በሸካ ዞን ለበርካታ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የሸካቾ ባህላዊ መዋቅራዊ አስተዳደር ስርዓት ዳግም ወደ ስራ እንዲገባ አድርገናል ብለዋል፡፡
የሸካቾ ባህላዊ መዋቅራዊ አስተዳደር ስርዓት ዳግም ወደ ስራ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ በርካታ ከባህልና ታሪክ ጋር ተያይዞ የሚለሙ ጉዳዮች ተለይተው የማልማት ስራ እየተከናወኑ እንዳሉ ያብራሩት ኃላፊው በዞኑ የሚገኙ ሶስት ነባር ብሔረሰቦች ማለትም የሸካቾ፣ የሸኮና የማጃንግ ተምሳሌቶችን በመለየትና በመመዝገብ ተሰንደው እንዲቀመጥ የማድረጉ ተግባር ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
የሸካ ዞን ከሚታወቅባቸው አንዱና ዋናኛው የእርቅ ስነ ስርዓት ነው፡፡ በዞኑ ዎራፎ የሚባል የእርቅ ስነ ስርዓት መኖሩንና የተለያዩ አለመግባባቶች፣ ወንጀሎች፣ ስርቆቶችና ክህዳቶች በሚኖሩበት ጊዜ ያለምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በአወጫጭኝ በሀገር ሽማግሌዎች ዘንድ እራሱን የሚያጋልጥበትና ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ እየጠየቀ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚቀላቀሉበት ስርዓት ነውም ብለዋል አቶ ተግባሩ፡፡
በስፖርት ዘርፍም እንደዞን በርካታ ተግባራት የተከናወኑ መሆናቸውን ያናሱት የመምሪያው ኃላፊ የ2016 ዓ.ም ክልላዊ የባህልና ስፖርት ፌስትቫል በዞኑ በማሻ ከተማ ማካሄዱን ተናግረዋል ፡፡
በውድድሩም አጠቃላይ ውድድር ሸካ ዞን በአንደኝነት ማጠናቀቁን አውስተው በማስ ስፖርትና በእግር ኳስ ተፎካካሪ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ቡድኖችን ለመፍራት የስፖርት መዘውታሪያ ስፍራዎችን ማሰመር እና ምቹ በማድረግ በርካታ ስራዎችን እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀውልናል፡፡
የትኛውም ባህልን ያላሳደገ አካባቢና ህብረተሰብ በኢኮኖሚውም ሊያድግ እንደማይችል የገለጹት አቶ ተግባሩ እንዳሸው ለዚህም ባህል ዋነኛው የኢኮኖሚ መሠረት ተደርጎ እንደሚወሰድና ባህልን በተገቢው ጠብቆና አልምቶ ለትውልድ ማሻገር በጣም መሠረታዊ ነው ብለዋል፡፡
ባህልንና የቱሪዝም ቦታዎችን መጠበቅና መንከባከብ የቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ እንዲሁም ለአንድ አካባቢ በኢኮኖሚም ሆነ ለፖለቲካው ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡


በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *