


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ጫሬ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሥድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በቀበሌው ትናንት ምሽት የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ ዛሬ ጠዋት 2 ሠዓት ላይ የመሬት መንሸራተት መከሰቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
በአደጋው ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች የሁለት ቤተሰብ አባላት ሲሆን ከአንደኛው ቤተሰብ አራት እንዲሁም ከሌላኛው ቤተሰብ ሁለት ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ አስረድተዋል፡፡
በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋም ሁለት ቤት መውደሙን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል፡፡
የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ እስከ አሁን 4 አስከሬን ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በአካባቢው አሁንም መሬቱ እየተናደ መሆኑ እና የውኃ ሙላት (ጎርፍ) መኖሩ የነፍስ አድን ሥራውን በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
