የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚያከናውነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ነገ ይጀመራል

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በተመለከተ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው እና ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በጋራ በቦንጋ ከተማ ተገኝተው ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነሮቹ በመግለጫቸው በምክክር ሂደቱ ቁልፍ ከሆኑ ተግባራት መካከል አጀንዳዎች አካታችና አሳታፊ በሆነ ሂደት የማሰባሰብ እንዲሁም በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች የማስመረጥ ተግባር በመሆኑ ለዚህም ኮሚሽኑ እስካሁን በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በአፋር እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራውን በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵ ህዝቦች ክልል መንግስት ደግሞ ከነገ ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እንደሚካሄድ የጠቆሙት ኮሚሽነሮቹ በክልሉ ከሚገኙ ከ57 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ተሳታፊዎች በምክክሩ እንደሚሳተፉ አብራርተዋል፡፡

ለመድረኩ ስኬት ኮሚሽኑየተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በቂ ቅድመ ዝግጅቶችን መድረጉን አብራርተው ለተሳታፊዎች ጥሪ መደረጉን፣ ከተወካዮቻቸውም አጀንዳዎችን እንዲያሰባስቡ መደረጉ፣ የመሰብሰቢያ እና የቡድን ውይይት ማካሄጃ ስፍራዎች እንዲሆኑና የፀጥታ እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችም የተጠናቀቀ መሆኑን በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡

ከነገ እሁድ ጥቅምት 24 እስከ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም ለተከታታይ 7 ቀናት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ በሚካሄደው በዚሁ ምክክር መድረክ የተለያዩ የማህበረሰብ መሰረቶችን የወከሉ ከ2ሺ 2 መቶ በላይ ተሳታፊዎች የሚመካከሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ 57 መዋቅሮች ከዚህ ቀደም በኮሚሽኑ የተለዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ሀገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሶስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ምሁራንና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዋነኛ ተሳታፊዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ተሳታፊዎች ተመካክረው አጀንዳዎቻቸውን በመለየትና በማጠናከር ለኮሚሽኑ የሚያስረክቡ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ ኮሚሽኑ የአጀንዳ የማሰባሰብ ተግባሩን አጠናቆና አጀንዳ ቀርጾ እንዲሄድ በሚደረገው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵ ህዝቦች ክልል የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ተወካዮች ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል።

ይህ ሂደት በራሱ እንደ ሀገር ላሉብን የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መሠረታዊ የሆኑ ምክንያቶች በምክክር የመለየት ባህልን ለማደበርና መፍትሔ ለመሻት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉም ኮሚሽነሮቹ በመግለጫቸው አብራርተዋል

ስለሆነም መላው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልነዋሪዎች ከጥቅምት 24 ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት የሚደረገውን የምክክር እና አጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሁም ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች የማስመረጡ ሂደት ያለው ከፍተኛ ፋይዳ በመረዳት ለሂደቱ ስኬት በምክሩ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *