የክልሉን ሠላም በዘላቂነት ለማጽናት የሚያበረታቱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

Spread the love

ይህ የተገለጸው የመልካም አስተዳደርና ህግ ጉዳዮች ዘርፍ ተቋማት የአፈጻጸም ሪፖርት በቀረበበት ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የአንደኛው ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።

የአፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የርዕሰ መስተዳድሩ

የመልካም አስተዳደርና ህግ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑ አቶ አክሊሉ ከበደ የሚያስተባብሯቸውን ተቋማት የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል ።

ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት በየተቋማቱ የሚያበረታቱ አፈጻጸሞች መኖራቸውን አመላክተዋል ።

በዚህም የክልሉን ሠላም በዘላቂነት ለማጽናት የሚያበረታቱ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ህገ_ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውርን ለመቆጣጠርም የተጠናከረ ስራ መኖሩን አመላክተዋል።

በሙስና እና ብልሹ አሰራሮች ሊመዘበር የነበረ የመንግስት ሀብትን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ማዳን መቻሉን በሪፖርቱ አመላክተዋል።

በቀረበው የተቋማት የአፈጻጸም ሪፖርት ከተሳታፊዎች አስተያየቶች እና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተነስተዋል ።

ከተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ባህላዊ ፍርድቤቶችን የማጠናከር፣ የከተማ የጸጥታ ስራዎችን የማጠናከር፣በማረሚያ ተቋማት ታራሚዎችን በተለያዩ ስልጠናዎች የማብቃት፣የወሳኝ ኩነቶች ምዘገባ የማጠናከር እንደሚገባ ተነስቷል።

የፐብሊክ ሰራተኞችን የመፈጸም አቅም ከመገንባት አንጻር፣ የትራፊክ ፖሊስ ህግ ከማስከበር አኳያ ክፍተት መታየት፣ ክልላዊ ገጽታን በሚዲያ ከማስተዋወቅ አንጻርም ትኩረት ተደርጎ ሊሰራባቸው ይገባል የሚሉ አስተያየቶች ተነስተዋል።

በተነሱት አስተያየቶች ከየተቋማቱ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

መድረኩን ያጠቃለሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልላዊ የሰላምና ጸጥታ ስራዎችን ለማጽናት የሰላምና ጸጥታ ፎረም ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።

ይህንንም ለማጠናከር አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የጸጥታ ችግሮችና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያን የማስፈታት ስራ ተጠናክሮ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

በህብረተሰቡ አካባቢ የሚሰሩ ስራዎችን በሚዲያ ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ሊሰሩባቸው እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

የፐብሊክ ሰርቫንቱ በየተቋማቱ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ተቋሙ ጠንክሮ ሊሰራበት እንደሚገባውም አሳስበዋል ።

በክልሉ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የሙስና ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ትኩረት በማድረግ ሊሰራበት እንደሚገባ በማሳሰብ መድረኩን አጠቃልለዋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *