


ለአገራዊ መግባባት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መሠረት እንደሆነና ያለ አገራዊ መግባባት ኅብረብሔራዊ አንድነት እንደማይጸና የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች አፈጉባኤዎች፣ ለኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች፣ ለሚዲያ አመራሮችና ጋዜጠኞች በበዓሉ መሪ ቃል ትንተና ላይ በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የተከበሩ አቶ አገኘሁ የወል ትርክቶች ተሰናስለውና ተዋሕደው ሲተገበሩ ኅብረብሔራዊ አንድነትን የሚገነቡ ሲሆን አገራዊ መግባባት በውይይት፣ በምክክር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ እንደሚመጣ ጠቅሰው የእኔ ባህል፣ የእኔ ታሪክ፣ የእኔ ሃይማኖት በአጠቃላይ የእኔ ማንነት ብቻ የሚለው ነጠላ ትርክት ግን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እውን እንደማያደርግ አስገንዝበዋል፡፡
እንደኛ ብዝኅ ሃይማኖት፣ ብዝኀ ቋንቋ፣ ብዝኀ ባህልና አመለካከት ላላት አገር ኅብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት አገራዊ መግባባቱ አስኳል እንደሆነ የጠቀሱት የተከበሩ አፈ ጉባኤው ለዘንድሮው በዓል ይህን መሪ ቃል መጠቀማችን የአገራቸንን ወቅታዊ ሁኔታዋንና ቀጠይ እጣ ፈንታዋን ያመለክትልናል በሚል እንደሆነ ጠቅዋል፡፡
የተከበሩ አቶ አገኘሁ በዓሉ የኢትዮጵያ ብዝኀ ማንነት ዕውቅና ከመስጠት በላይ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነታችንንና ሰላማችንን ለማጽናት፣ የፌዴራል ሥርዓታችን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ሁሉ በመነጋገርና በመመካከር በመፍታት ኅብረብሔራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው አንድነቷ ያልተጠበቀና ሰላሟ ያልሰፈነ አገር፣ ልማቷንና ማኅበራዊ እድገቷን ማሳካት አይቻላትም ብለዋል፡፡
ብዙኃን መገናኛ በዓሉ በሕዝቦች እምቅ ባህላዊ ዕሴቶች እየተገነባና በፌዴራል ሥርዓቱ እየዳበረ ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ እንዲሸጋገር ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው አስታውሰው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመቻቻል፣ በመከባበርና በመረዳዳት እንዲሁም በፍትሐዊነት ኅብረብሔራዊና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ በሚያስችሉ የሚዲያ ዝግጅቶች ላይ አቅደው መሥራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸዉን የፌደሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
