








የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የክልሉን የፍትህ ዘርፍ ተቋማት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ አፈጻጸም እንዲሁም በባህላዊ ዳኝነት ሥርዓት ዙሪያ ከባስደርሻ አካላት የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በክልሉ ያሉ የፍትህ ተቋማት የለውጥ ትግበራን በማሳለጥ ቀልጣፋና ፈጣን የፍትህ አግልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በዚህም የተገልጋዩችን እርካታ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የፍትህ ማሻሻያው ከፍ/ቤቶች አንጻር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ፈጣን መፍትሔ በማስቀመጥ ለዜጎች ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ተገማች የዳኝነት አግልግሎት ለማሰጠት ያስችላል ያሉት ዋና አፌ-ጉባኤው የለውጥ ትግበራውን በተሟላ መልኩ ለመፈጸም በሚደረገው እርብርብ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
የፍትህ ዘርፍ ተቋማት የለውጥ ትግበራው
በፍትህ ተቋማት የሚስተዋለውን የአግልግሎት ጥራት መጓደል እና የሥነ-ምግባር ችግር በመቅረፍ በተገልጋይ ህብረተሰብ ዘንድ የሚነሱ የቅሬታዎችን ለመፍታት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የክልሉ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ የገለጹት።
ክልላዊ የፍትህ ተቋማት የለውጥ ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ በ2015 በጀት ዓመት ማገባደጃ ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት ኃላፊው በዚህም መሠረት የተግባር አፈጻጸሙን የስትርግ ኮሚቴው በየጊዜው እየገመገመ መቆየቱን አመላክተዋል።
10 ዋና ዋና አምዶችና 61 ዝርዝር ተግባራትን መሠረት አድርጎ በተቀረጸው የክልሉ የሶስት ዓመት የፍትህ ማሻሻያ ትግበራን መነሻ በማድረግ የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚመልስ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅተው በምክር ቤት ፀድቆ ወደ ተግባር መገባቱን ነው ኃላፊው የገለጹት።
ከዚህም በተጨማሪ በማሻሻያው መነሻ ከመደበኛ የፍትህ አግልግሎት በተጓዳኝ ማህበረሰብ አቀፍ የፍትህ አግልግሎት እውቀና በመስጠት ወደ ተግባር እንዲገባ አሰራር በመዘርጋት በህግ ደረጃ በምክር ቤት መጽደቁን የገለጹት አቶ እሸቱ በረቂቅ ህጉ ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፈጠር ወደ ተግባር እንዲገባ የባለድርሻ አካላት ትኩረት መጠናከር እንዳለበት ጠይቀዋል።
በመድረኩ የክልሉ የብሄረሰቦች ምክር ቤት አፌ-ጉባኤ አቶ መቱ አኮ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማርያምን ጨምሮ የፍትህ ዘርፍ የክልልና የዞን መዋቅር አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን ዝርዝር የእቅድ አፈጻጸምና የ2017 የዘርፉ እቅድ እየቀረበ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
