በተከናወነዉ ሰፊ ርብርብ የወባ በሽታ ጫና ባለፈው ከነበረበት የቀነሰ ቢሆንም አሁንም ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

Spread the love

የክልሉ ጤና ቢሮ ሁሉተኛ ዙር ቀበሌን መሠረት ያደረገ የወባ በሽታ የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻ በይፋ አስጀምሯል።

ዘመቻውን በይፋ ያስጀመሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በሮው ሌሎች የባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ባከናወናቸው ሰፊ ርብርብ የወባ በሽታ ጫና ባለፈው ከነበረበት የቀነሰ ቢሆንም አሁንም ጠንካራ ስራ እንደሚያሰፈልግ ገልጸዋል።

የሚፈለገውን ግብ ለመድረስ ሁለተኛ ዙር ዘመቻ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው በዘመቻው ቀበሌን፣ ጤና ኬላንና ጤና ጣቢያዎችን ማዕከል በማድረግና የህብረተሰቡን ተሳታፊነት በመጨመር ውጤታማ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል ።

አሁን ካለበት የወባ በሽታ ታማሚ ቁጥር በ50% እንዲሁም የሞት ምጣኔ 90% መቀነስ የዘመቻው ግብ እንደሆነም ተብራርቷል።

አሁን ያለንበት ወቅት ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ጊዜ ስለሆነ ህብረተሰቡ የወባ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን ሳይዘናጋ ተግባራዊ ልያደርግ እንደሚገባም አቶ ኢብራሂም አብራርተዋል።

ቢሮው ከመከላከልና ከመቆጣጠር ተግባራት በተጨማሪ የመረጃ ጥራት ማስጠበቅና ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ታውቋል።

በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ማህበረሰቡን የማነቃነቅ ተግባር እንዲሁም ለበሽታው መከላከልና መቆጣጠር የሚያደርጉትን ድጋፍና ክትትል ማጠናከር ያስፈልጋልም ተብሏል።

ለወባ በሽታ መከላከልና ለሌሎች የጤና ተግባራት ስኬታማነት በየደረጃው ያሉ የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀቶች በንቃት መሳተፍ ይገባቸዋልም ተብሏል።

ጤና ኬላዎች ዘውትር ክፍት ሆነው ህብረተሰቡን ማገልገል ይገባቸዋል ያሉ ኃላፊው የጤና መረጃዎች በወቅትና በጥራት ለሚመለከተው አካል ልቀርብ ይገባልም ብለዋል።

ከወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ጎን ለጎን መደበኛ የጤና አገልግሎትና የክትባት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥል የገለፁት አቶ ኢብራሂም ሁሉም የዘመቻ እና መደበኛ ስራዎች መረጃ በተቋቋመው በየዕለቱ እንደሚላክ አስረድተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *