ወጣቶች በተሰማሩባቸው የስራ መስኮች ውጤታማ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፦ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

Spread the love

በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች በተሰማሩባቸው የስራ መስኮች ጥራት ያለውና በገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ክልላዊ የክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ የንቅናቄ መድረክ እንደቀጠለ ነው።

በንቅናቄው መድረክ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በክልሉ በርካታ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች መኖራቸውን ተናግረው ኮሌጆች በሚሰጡት ስልጠናዎች የአካባቢውን ጸጋ በመጠቀም ፍላጎትና ገበያን መሠረት አድርጎ ከማሰልጠን አኳያ ወጥ የሆነ አሰራር አለመኖሩን አመላክተዋል።

በክልሉ በጥናት ላይ የተመሠረተ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የአካባቢውን ጸጋ መሠረት ያደረገ ክልላዊ እይታ ኖሯቸው ወጣቶችን ማሰልጠን እንደሚገባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

በክልሉ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግሮችን መቀነስ የሚቻለውም ክህሎት መርና ገበያ መር ስልጠና አግባቦችን በመጠቀም ሊሆንም ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

በኮሌጆች ሰልጥነው ወደ ስራ የተሠማሩ ወጣቶች

በተሰማሩባቸው የስራ መስኮች ውጤታማ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል ።

በዘርፉም የተሰራጨ ብድር አመላለስና ስርጭት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰራባቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የስራ ስምሪት እንዲሁም በኢንዱስትሪዎች ተቀጣሪ በሆኑ ዜጎች በሚደረገው የስራ ስምሪት ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል።

የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው በበኩላቸው ወጣቶችን በስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከሌማት ትሩፋት እና ከኮሪደር ልማት ስራዎች ጋር በማስተሳሰር መስራት ይገባል ብለዋል።

የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በኮሌጆች የአካባቢውን ጸጋ መሠረት ያደረገ ስልጠና በየኮሌጆች እንዲዘረጋ ትኩረት ይደረጋልም ብለዋል።

በክልሉ ስራአጥነትን ለመቀነስ ከዚህ ቀደም የተሰራጩ ብድሮችን የማስመለስና ብድር የማሰራጨት ስራ መሠረታዊ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩበት ይገባልም ብለዋል።

በመድረኩ በቀጣይ ወቅት ትኩረት የሚሰጡባቸው የተለያዩ የንቅናቄ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

በዚህ የንቅናቄ መድረክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *