




የበለፀገች ሀገር የመገንባት ህልማችንን ለማሳካት ተቋማት ከእቅድ በላይ መፈፀም አለባቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆኑ አስፈጻሚ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተገምግሟል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለተቋማት ግንባታ በተሰጠው ትኩረት በርካታ ሀገራዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
ለአብነትም ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆኑ ተቋማት በተለይም የልማት ድርጅቶች ከኪሳራና ከሀብት ብክነት ተላቀው ወደ ትርፍና ትልቅ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅምነት ተሸጋግረዋል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ተሟላ ትግበራ መግባቱን ተከትሎ በገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደርና በውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ውጤት ማሳያ መሆናቸውን አንስተዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
በቀጣይም የስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ሙስና እና መሰል ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም ወደ ኋላ የቀሩ ዘርፎችን በልዩ ትኩረት ማካካስ፣ የሪፎርም ሥራዎችን ማሳለጥ፣ የመረጃ ጥራትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የበለፀገች ሀገር የመገንባት ህልም እውን የሚሆነው ተቋማት ከእቅድ በላይ መፈፀም ሲችሉ እንደሆነም ገልጸዋል።
በተለይም ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆኑ ተቋማት አመራሮች ሌት ተቀን መትጋት፣ ጀምሮ መጨረስን ማስፋት፣ ፍጥነትና ፈጠራን ማጠናከር እና ለሌሎች አርዓያ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ በበኩላቸው፥ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ የመጠቀም እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ በተለይ በጥቁር ገበያ የተገኘ የውጭ ሀገር ገንዘብን በሀሰተኛ የባንክ ሰነድ ህጋዊ ለማስመሰል የሞከሩ በርካታ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመግታት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ትግበራ ለማሳካት የፋይናንስ ዘርፉን ከህገወጥ እንቅስቃሴዎች የመጠበቅ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፥ በሩብ ዓመቱ ከፓስፖርት ተደራሽነትና ህትመት አኳያ የተሻለ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ተከትሎም የቪዛ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ እየሰራን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ፥ በሩብ ዓመቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያን ጸጋዎች በማስተዋወቅ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ ለማድረግ እየመጡ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ መሠራቱን ጠቅሰው፥ በቀጣይም የተያዘውን ሀገራዊ ግብ የሚያሳኩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
