



የወባ ወረርሽኝ ስርጭት ለመግታት “ረቡዕን ለወባ” የሚል የጽዳት ዘመቻ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
እንደ ሀገር የወባ ወረርሽኝ በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የግልና የአካባቢ ጽዳት ዘመቻ ሲደረግ መቆየቱ ይታወቃል።
ይህንን አምራቹን ኃይል እየጎዳ ያለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል እንደ ካፋ ዞንም ይሁን እንደቦንጋ ከተማ የተለያዩ የጽዳትና የማፋሰስ ሥራዎች ዛሬም እየተሰሩ ይገኛሉ።
በዚህ መነሻ “ረቡዕን ለወባ” በሚል ዛሬ ማለዳ የዞን ከፍተኛ አመራሮች፤ የቦንጋ ከተማ አመራሮች ፤የጤና ባለሙያዎችና የተለያዩ የከተማ ነዋሪዎች ተገኝተው በሸታ ዙሪያ ቴክኒክና ሙያ አካባቢ ተዳፋት የሆኑና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማሽንና በሰው ኃይል ታግዘው የማፋሰስ ሥራ ተሰርቷል።
በዚህ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት የጤና ባለሙያዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ወባ በማህበረሰቡ ህይወትና ጤና ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ጫና ገልፀው ይህንን አስከፊ በሽታ ሁሉም አካባቢውን በማፅዳትና ፍሳሽ በማስወገድ ወባን መከላከል ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በተጨማሪ የጤና ተቋማትና የዘርፉ ባለሙያዎችን ጨምሮ የከተማው ነዋሪ በሙሉ የወባን ስርጭት ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው አካባቢን ከማጽዳት በተጨማሪ በመንግስት በኩል የአጎበር ስርጭትና የኬሚካል ርጭትም ጉዳይ ልዩ ትኩረት መሰጠት ያለበት መሆኑን አስምሯል።
የካፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አጥናፉ ኃይሌ በዘመቻው ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ወባ እንደሀገርም ይሁን በአካባቢያችን ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረና የአምራቹን ኃይል ጤና እየጎዳ መሆኑንና በህብረተሰቡ ላይ ያልተገባ የኢኮኖሚ ኪሳራ እያስከተለ ያለ ወረርሽኝ በመሆኑ በመከላከሉ ሥራ ላይ ሁሉም መረባረብ አለበት ብሏል ።
አቶ አጥናፉ ኃይሌ አክለው ባስተላለፉት መልዕክት የወባ ስርጭት መልኩን እየቀያየረ አንዳንድ ጊዜ የመጨመር፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን አንስተው ለዚህም ምክኒያት የሚሆነው ቀጣይነት ባለውና ባልተቆራረጠ መልኩ የግልና የአካባቢ ንጽህናን ያለመጠበቅና “ረቡዕን ለወባ” ተብሎ የተጀመረው ንቅናቄ መቀዛቀዙ ነው ብሏል።
በቀጣይ በየደረጃው ያለው አመራርና የከተማው ነዋሪ በሙሉ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠርና “ረቡዕን ለወባ” ተብሎ የተጀመረውን ዘመቻ በማቀጣጠል በሰው ህይወትና በሀገር ልማት ላይ አደጋ እየደቀነ ያለውን የወባ ወረርሽኝ መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ አጥናፉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባው አቶ አስማማው አደመ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር የወባ ወረርሽኝ በየጊዜው በማህበረሰቡ ጤንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩንና የአምራቹን ኃይል ኢኮኖሚ በእጅጉ እየጎዳ ነው በማለት ይህንን በሽታ ለመከላከል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ማህበረሰቡ መደገፍ አለበት ብሏል።
አቶ አስማማው አክሎ በከተማው “ረቡን ለወባ” ተብሎ የተጀመረው የጽዳት ዘመቻ በተወሰነ መልኩ መቀዛቀዙ የወረርሽኙን ስርጭት እያባባሰው ይገኛል በማለት ይሄው የግልና የአካባቢ ጽዳትና ውሃ ያቆሩ አካባቢዎችን የማፋሰስ ተግባር በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበ ብሏል። ለዚህም ከጤና ተቋማት ጀምሮ በየደረጃው ያለው የአመራርና የከተማውን ነዋሪ ርብርብና ዕገዛ አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
