ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን “ህፃናት የሚሉት አላቸው እናዳምጣቸው! ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተገለጸ

Spread the love

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገልጿል ፡፡

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ

ወ/ሮ ገነት መኩሪያ እንደገለጹት ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አካል የሆነው የአለም ህጻናት መብቶች ኮንቬንሽን እ.ኤ.አ ኑቬምበር 20/1989 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ፀድቆ በስራ ላይ እንዲውል መደረጉን ተከትሎ ዕለቱ ስምምነቱን በፈረሙ ሀገራት ዘንድ ታስቦ እንዲውል በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ቀኑ ከየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተገናዘበ መልኩ በየዓመቱ እየተከበረ እንደሚገኝ አንስተዋል ፡፡

በዓሉ ዘንድሮ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ “Listen to the Future” በሀገራችን ኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ በክልላች ለ3ኛ ጊዜ “ህፃናት የሚሉት አላቸው እናዳምጣቸው!” በሚል መሪ ቃል የክልሉ ማጠቃለያ መድረክ ህዳር 8/2017 ዓ/ም በቦንጋ ከተማ ይከበራል ተብሏል።

በዓሉ በዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በት/ቤቶች ደረጃ ህፃናትን፣የህፃናት ፓርላማ አባላት፣ምህራንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በልዩ ልዩ መርሃ-ግብሮች ሲከበር እንደቆየ ቢሮ ኃላፊዋ አክሏል።

በዓሉም ሲከበር ስለ ህፃናት መብቶች፣ ስለ ህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ በህፃናት ላይ ስለሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ጥቃቶች እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያ በህፃናት ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ዙሪያ ሰፊ ውይይት የተካሄደበትና ግንዛቤ ማስጨበጥ መቻሉን ኃላፊዋ ገልጿል ፡፡

በዚህም የማጠቃለያ መድረክ የዓለም አቀፍ የህጻናት ቀንን የህጻናት መብቶችን በማስተዋወቅ፣ በክልላችን ከተከሰተው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎችን ድጋፍ በማድረግ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፣ ድጋፍ በማድረግና በተለያዩ ፕሮግራሞች በዓሉን በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ የሚመለከተቻው የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የህፃናት ተወካዮች፣ የክልሉ ህፃናት ፓርላማ አመራሮችና አባላት የሚሳተፉበት መድረኩን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቁን የቢሮ ኃላፊዋ መግለጻቸዉን የቢሮዉ መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *