



ኩባንያው የአገልግሎት አሰጣጡን የማዘመንና ቅርንጫፍ ጸ/ቤቶችን በየክልሎች የመክፈት ጉዳይ ትኩረት ይሰጠዋል ተብሏል።
ኩባንያው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ በዛሬው ዕለት በይፋ ከፍቷል።
በክልሉ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት መክፈቻ ስነ_ስርዓትን ተከትሎ የኩባንያውን የአፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ባቼ በ4 ክልሎች በ67 ከተሞች ተደራሽ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
ኩባንያው በክልሎቹ 976 ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ከ408 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸውን የሊዝ ማሽነሪዎችን ማቅረብ መቻሉንም አብራርተዋል ።
ደቡብ ካፒታል ኩባንያ ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ያሰራጨውን ብድር 96 ከመቶ ማስመለስ የቻለ ኩባንያ መሆኑንም አቶ ታረቀኝ አብራርተዋል ።
የኩባንያው አጠቃላይ ካፒታል 591 ሚሊዮን መድረሱንም አቶ ታረቀኝ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ለጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ቀጣይነት ባለው መልኩ ዕድገት በማምጣት በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል ።
ኩባንያው በስራ ዕድል ፈጠራና በእንዱስትሪ ልማት እያበረከተ ያለው አሰራር ጣይነት እንዲኖረው ባለድርሻ አካላት ንቁ፣ቀልጣፋና ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኩባንያውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ የተመለከተ የመወያያ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ምህረቱ ዮሴፍ ኩባንያው ሀብትና የስራ ዕድል በመፍጠር በኩል ሀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል ።
ኩባንያው ቀጣይነት እንዲኖረውም የተሰራጩ ብድሮችን ማስመለስ፣አባላትን ማፍራትና ከአበዳሪ ድርጅቶች ፈንድ በማፈላለግ ብድር የማሰራጨት ስራዎችን ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ አመላክተዋል ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተሰራጨው ብድር እስከ አንደኛው ሩብ ዓመት 93 ከመቶ ብቻ ብድር መመለሱንም አቶ ምህረቱ አብራርተዋል ።
በ2017 በጀት ዓመት በ4ቱ ክልሎች ለካፒታል ዕቃዎች ግዢ 566.7 ሚሊዮን ብር ብድር ለማሰራጨት መታቀዱንና ከዚህም ውስጥ 87.84 ሚሊዮን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለማሰራጨት ታቅዷል ብለዋል።
ኩባንያው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፣በደቡብ ኢትዮጵያ ፣በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በሲዳማ ክልሎች ሰፋፊ መሰረት የሚጥሉ በማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አብራርተዋል ።
በቀረበው የመወያያ ሰነድ ተሳታፊዎች አስተያየቶች እና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ለተነሱት አስተያየቶችም ከኩባንያው የቦርድ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቷል።
የደቡብ ካፒታል ኩባንያ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ኩባንያው የትናንት የጋራ አሻራ ፣የጋራ ማደጊያችን የነጊያችን ፋና ነው ብለዋል።
በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ በማድረግ ብቸኛ የፖሊሲ ተቋም መሆኑንም አቶ ስንታየሁ አንስተዋል ።
ይህንን ተከትሎም ኩባንያው እስከ 2014 ዓ/ም 123 ሚሊዮን ብር ብድር ማሰራጨቱንና የሪፎርም ስራዎች ከተሰሩ በኋላ በ2016 ዓ/ም ብቻ 385 ሚሊዮን ብር ለካፒታል ዕቃ ማበደር መቻሉንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኩባንያው የማበደር አቅሙ 8 ሚሊዮን ደርሷል ያሉት አቶ ስንታየሁ በክልሎች መካከል ተቋማዊ አገልግሎት ተደራሽነቱንና የሚሰጠውን አገልግሎት ፍትሐዊነት ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመንና ቅርንጫፍ ጸ/ቤቶችን በየክልሎች የመክፈት ጉዳይ አንዱና ዋነኛም ነው ብለዋል።
በታጠቅ አበበ
