ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የተከተለችው መርህ ለቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው

Spread the love

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የተከተለችው የሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲያዊ መርህ የቀጣናውን ሀገራት ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እያደገ ላለው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የወደብ ቁጥርን ማስፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የባህር በር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ብልጽግና ወሳኝ እንዲሁም ለጎረቤት ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንና በጋራ የመልማት አቋምን በማጠናከር በቀጣናው ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ይህ የባህር በር ላላቸው ጎረቤት ሀገራትም የበለጠ እድገትና ልማትን የሚያረጋግጥ እንደሆነ በአፅንኦት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መልማት፣ ብልጽግና እንዲሁም መረጋጋት የጎረቤት ሀገራትንም ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በትብብር ቀጣናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በደቡብ ሱዳን ጁባ ዩኒቨርሲቲ ሰላም ኢንስቲትዩት የሰላምና ጸጥታ መምህር ቴር ማጆክ (ዶ/ር) ቀጣናዊ ትብብር ለጋራ ተጠቃሚነትና ልማት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ እያደገ የሚገኘውን የህዝብ ቁጥር ፍላጎትና የገቢና ወጪ ንግድ አገልግሎት መሸከም የሚችል አማራጭ ወደብና የባህር በር ለማግኘት የተከተለችው አማራጭ ተገቢና ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗ ባለፈ፣ ለቀጣናው ሰላምና ጸጥታ ያላትን አስተዋፅኦ በምጣኔ ሃብት ትስስር ለማጠናከር እየሄደችበት ያለውን መንገድ አድንቀዋል።

ቀጣናዊ ትስስርን እውን ለማድረግ ሀገራት በትብበር ሊሰሩ እንደሚገባ የጠቆሙት ዶክተር ቴር ማጆክ፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ ሚና እየተወጣች ስለመሆኑ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላምን በማጠናከር ልማትና ብልጽግናን እውን ለማድረግ የጀመረችውን የተግባር እርምጃ ዋጋ መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *