ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆን አሻጋሪ ሃሳብ በማመንጨት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

Spread the love

ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈቱና ለትውልድ የምትመች አገር ለመገንባት የሚያስችል አሻጋሪ ሃሳብ በማመንጨት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

” ተመካክረን ኢትዮጵያን እንገንባ፤ እኔም ለሀገሬ እመክራለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባዘጋጀው መድረክ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ተዋቂ ግለሰቦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ እንደገለጹት፤ እስካሁን በተለያዩ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተከናውኗል።

በኦሮሚያ ክልል ከታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ከሰባት ሺህ በላይ የማህበረሰብ ተወካዮች መሳተፋቸውን አውስተዋል።

ከነዚህም መካከል የክልሉን ማህበረሰብ ወክለው በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ 320 ተወካዮች መምረጣቸውንም አስታውቀዋል።

አጀንዳ የማሰባሰቡ ሂደትም ነፃና ዴሞክራሲያዊ በመሆነ መንገድ መከናወኑን አስረድተዋል።

ከፖለቲከኞች ፣ ከተዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችጋር ጋር እየተካሄደ ያለው መድረክም ለአገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆን ሀሳብ ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች አገርን የሚያሻግር ሀሳብ በማመንጨት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አገርን ለማሻገር የሃሳብ መሪዎችና በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች አገር ለመገንባት የሚያስችል አሻጋሪ ሃሳብ ማመንጨት ይገባል ነው ያሉት ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *