




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እና የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አስተዳደር የታርጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን እና ሶሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክብርት ሚኒስትር ደኤታ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ወርዶ ማየታቸው ለትምህርት የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ መምህራንና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት ጠንክሮ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ለታርጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ለሶሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህት ቁሳቁስ በለገሱበት ወቅት የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት አግኝተው ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የባድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
የሀገር ሽማግሌ አቶ ተረፈ ገብሬ በበኩላቸው በመምህራን በኩል የተሻለ የሰው ኃይል ቢኖርም ትልቁ ችግር የግበዓት እጥረት ለትምህርት ቤቱ መኖሩን ተናግረው አሁን ለተደረገው ድጋፍ ሚኒስትር ዴኤታዋን አመስግነዋል።
በጉብኝቱ ላይ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ሚኒስትር፣ የክልልና የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
