
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ወራት አምራች ኢንዱስትሪዎች 816 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች ማምረታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ለአምራች ኢንዱስትሪው ያመጣው መልካም ዕድል፣ ተግዳሮት እና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ የመንግሥትና የግል ዘርፉ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የማምረቻ ኢንዱስትሪውን በመደገፍ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በትኩረት ሰርቷል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እና የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት እድል ፈጥረዋል ብለዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የነበረውን ማነቆ ለመፍታት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአስር ዓመት መሪ የልማት እቅዱን መነሻ ያደረገ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ፖሊሲው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ገበያ ታሳቢ ያደረጉ እና ማምረቻ ኢንዱስትሪው በግሉ ዘርፍ እንዲመራ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪው ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ባለፉት ሶስት ወራት 816 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ማምረት መቻሉን ነው የጠቀሱት።
በዚህም በኢትዮጵያ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቀላል ከውጭ ማስገባት ደግሞ ከባድ የሆነበት አውድ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
የአምራች ኢንዱስትሪው በፖሊሲ ማነቆ ምክንያት ቀላል የሆኑ ነገሮች ሁሉ ውድና ከባድ ሆነውበት መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተዘግተው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ እና የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ለውጭ ገበያ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የአምራች ኢንዱስትሪውን የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ከፍ ማድረግም ተችሏል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
