



3ኛው የቤንች ብሔር ምሁራን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት አለም ለዛሬ ስልጣኔ ፣ ዘመናዊነትና ዕድገት የበቃችው በምሁራን የፈጠራ ፣ የጥበብና የምርምር ስራዎች ታግዛ ነው ብለዋል።
ዛሬ ላይ በአለማችን እጅግ ሰለጠኑ ፣ በሳይንስና ቴክሎጂ ምጡቅ ሆኑ የሚባሉት ሀገራት ከመሬት ተነስተው ሳይሆን ለትምህርት ፣ ለጥናትና ምርምርና ለፈጠራ ስራዎች በሰጡት ልዩ ትኩረትና ዜግቻቸውን የዕውቀት ባለቤት በማድረጋቸው ነው ብለዋል።
ምሁራን ለአንድ ሀገር ፣ ህዝብና ማህበረሰብ በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ችግር ፈቺ የጥናት ምርምር እንዲሁም ዘላቂ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ሰላምን በማስፈን ፣ ልማት ፣ ዕድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥና የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የሙህራን ማህበራት ሚና የጎላ ድርሻ አለው ብለዋል።
መደራጀት ፣ መተባበርና ለጋራ ሀሳብና ተጠቃሚነት መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ በርካታ ተሞክሮና ልምዶችን አይተናል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ምሁራን የሀገር ዋልታና ካስማ ፣ የጥበብ ፣ የዕውቀትና የችግር ፈቺ ምርምርና ጥናት መፍለቂያ ማዕከላት ናቸው ብለዋል።
ምሁራን የህዝቡ አጀንዳ አጀንዳችን ከሆነ ከመነጣጠል ፣ ከመገፋፋትና ከመበተን ይልቅ የጋራ አስተሳሰብ አንድነትን በመፍጠር በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የቤንች ብሔር ምሁራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታሁን ተክሌ እንደተናገሩት የምሁራን ማህበሩ የብሔሩን ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ማጠናከርና ማስፋትን አላማ አድርጎ መመስረቱን ገልጸዋል። ባለፉት 6 አመታትም በብሔሩ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ውሳኔዎችን እየወሰነና እየተገበረ እዚህ መድረሱንም ገልጸዋል።
ምሁራን በሀገር ሰላም ፣ ልማት ፣ ዕድገት እና በማህበረሱ ተጠቃሚነት ላይ ጉልህ ሚና አላቸው ያሉት አቶ ጌታሁን የብሔሩ ምሁራን ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ ራሳቸውና አካባቢያቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ አትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የማህበሩ አባል አቶ ፀጋዬ ማሞ በዙም ባስተላለፉት መልዕክታቸው ሳይማር ያስተማረን ህዝብ የሰላም ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምሁሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመስራት ሊያግዝ ይገባል ብለዋል። በተናጠል የሚገኙ ዕውቀቶችን ማቀናጀት ፣ ማስተሳሰርና ለጋራ ጥያቄዎች የጋራ መልስ ለማግኘት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የብሔሩ ተወላጅና በስራ ምክንያት በሌላ አካባቢ የሚገኙት አቶ ማዕረጉ ሀብተማርያምም በዙም ገብተው መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።
