




የኢትዮጵያ ሜትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት በመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በክልሉ የሜትሮሎጅ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ ማቋቋም ላይ መነሻ ያደረገ የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ሜትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥነት ያላቸው መረጃዎችን በመሰብሰብ በማደራጀትና በመተንተን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ስራዎችን የሚሰራ ተቋም ነው።
ኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን በሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ለጤና፤ግብርና፤አደጋ ስጋትና ስራ አመራር፤አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ እንዲሁም በሌሎች ተቋማት ምክረ ሀሳብ የማቅረብ ሥራ እየሠራ ነው።
ኢንስቲቲዩቱ በመላ ሀገሪቱ ከ1 ሺህ 372 የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን እነዚህም በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በ15 ደቂቃ ውስጥ መረጃ አደራጅቶ ወደ ቋት የማስገባት ደረጃ ላይ የደረሱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስትር ጋር በመተባበር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚቋቋመው የሜትሮሎጅ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ አምስት የአርብቶ አደር ወረዳዎችን የሚያቅፍ እንደሆነም ተናግረዋል።
ይህም በ250 ኪ/ሜ ራድዬስ የሜትሮዎሎጂ መረጃዎችን በ15 ደቂቃ ውስጥ ወደ መረጃ ቋት ሊያስገባ የሚችል መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አከባቢዎች የዚሁ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አከባቢ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው በክልሉ የሜትሮዎሎጂ መሰብሰቢያ ጣቢያ መቋቋሙ በአርብቶ አደር አከባቢዎች ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምክረ ሀሳብ ለመሰጠት አስተዋጽኦው የጎላ በመሆኑ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ወቅቱን የጠበቀ ሜትሮዎሎጂ መረጃ መሰብሰብ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎችን በመከላከል ረገድ ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ ይጠበቃል ብለዋል።
የምዕራብ ኦሮሚያ ሜትሮዎሎጂ ማዕከል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ገመቹ ራጋ ማዕከሉ የሜትሮሎጅ ጣቢያዎችን የማቋቋም፣ማጠናከርና የጣቢያ ቅኝት ስራዎችን ጨምሮ መረጃ በመሰብሰብ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፌዴራል፣ የክልልና ሌሎች የሚመለከታቸው የዞንና የወረዳ ባለ ድርሻ አካላት በመድረኩ ተሳትፈዋል።
በፍቅር ከበደ
