************








“ቆይታ ከእኛ ጋር” እንግዳችን ፕሮግራም
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታመነ በቀለ በሌማት ትሩፋት አጀማመር ፣ የትኩረት መስኮች፣ ዓላማ፣ ለዘርፉ በተለያዩ አካላት የተደረጉ ድጋፎች፣ የተመዘገቡ ውጤቶችና የታዩ ለውጦች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል!
መንግስት ኮሙኒኬሽን (መ/ኮ)፡ የቆይታ ለእኛ ጋር ፕሮግራም እንግዳ ለመሆን ፍቃደኛ ስለሆኑ ከልብ እናመሰግናለን።
አቶ ታመነ በቀለ፣ እናንተም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
(መ/ኮ)፦እንደክልላችን የሌማት ትሩፉት መቼ ጀምሯል?
አቶታመነ፦ እንደሀገር በክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በሀገርም ሆነ በክልላችን 2015 ዓ/ም ዓ/ም ተጀምሯል ።
(መ/ኮ)፦ ኢንሼቲቩ ምንን ዓላማ አደርጎ እንደጀመረ ቢያብራሩልን?
አቶ ታመነ፦ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ዘርፉን በማጠናከር የስነ ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል፣ ስራ ዕድል ለመፍጠር እና ከውጭ የሚመጣውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት፣ በእንስሳት ዘርፍ የኤክስፖርት ምርትን ማሳደግን ዓላማ በማድረግ ነው የተጀመረው።
መ/ኮ ፦ የሌማት ትሩፋት ምን ምንን መሠረት አደርጎ ነው የተጀመረው?

አቶ ታመነ፦ እንደ ሀገር በአራቱ ኢንሼቲቭ ዘርፎች ማለትም በወተት፣ በዶሮ፣ በማር፣ በዓሣ ለመጀመር አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም የክልላችን ዕምቅ አቅምን በመለየትና ታሳቢ በማድረግ በቀይ ስጋ በመጨመር በአምስቱ ዘርፎች ማስጀመር ተችሏል ።
መ/ኮ፦ እንደ ክልላችን የት የት ተጀምሯል ?
አቶ ታመነ፦ይህ ተግባር አፈጻጸም ከዞን ዞን፣ ከወረዳ ወረዳ እንዲሁም ከመንደር መንደር የሚለያይ ቢሆንም በክልሉ በስድስቱም ዞኖችን የመልማት አቅምና ነባራዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ ተጀምሯል።
የእያንዳንዱን ኢንሼቲቭ አፈፃፀሙን በምናይበት ጊዜ ወተት በ31 ወረዳ፣ ዶሮ በ40 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር፣ ማር በተመረጡ በ27 ወረዳዎች የቀይ ስጋ ማሞከትና ማድለብ በ22 ወረዳዎች እንዲሁም ዓሣ በ14 ወረዳዎች ማስጀመር ተችሏል ።
ለዚህም ስራ ሲባል በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት በየወረዳው ቀበሌዎችን በመምረጥ ሞዴል መንደሮችን የመፍጠር ስራ እየተሰራ ይገኛል ።
በዚሁ መሠረት ከ50- 120 አርሶ አደሮች አንድ የወተት መንደር፣ ከ50-100 አርቢዎች አንድ የዶሮ መንደር፣20 አርቢዎች/ አናቢዎች አንድ የማር መንደር ፣ 15 አስጋሪዎች አንድ የዓሣ መንደር እንዲሁም 30 አርቢዎችን አንድ የቀይ ስጋ መንደር ስታንደርዱን በማስቀመጥ ታቅዶ በመሠራት ላይ ይገኛል ።
ይሁን እንጂ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት በየመንደሩ የተቀመጠውን የአባወራ ብዛት እና የጥራት ጉዳይ አንደ በማሳካት ተጠቃሚ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአራት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማሣካት ግብ ተጥሎ እየተሰራበት ይገኛል።
መ/ኮ፦ የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ወዲህ በክልላችን የመጡ ለውጦች ብጠቅሱ?
አቶ ታመነ፦ የሌማት ትሩፋት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተመዘገቡ ውጤቶችና የመጡ ለውጦችን በምናይበት ጊዜ የወተት ምርት በ2015 ዓ/ም 307 ሚሊየን ሊትር ከነበረበት በ2018 ዓ/ም 559 ሚለየን ሊትር ለማድረስ ግብ የተጣለ ሲሆን አሁን 380 ሊትር ማድረስ ተችሏል ። ለዚህም በምክንያታዊነት አዳዲስ የተሻሻለ ዝሪያ ያላቸው የወተት ላሞችን ገስቶ የማስገባትና የእርባታ ጣቢያዎች መከፈታቸው ነው።
በዝሪያ ማሻሻል በ2015 ዓ/ም 17,000 እንስሳትን ማዳቀል የተቻለ ሲሆን በ2016 ዓ/ም 33,000 ፣ በ2017 ዓ/ም 75,000 ለማዳቀል ታቅዶ በአምስት ወራት ውስጥ 20,900 ደርሷል።
በዶሮ እርባታ በክልሉ ውስጥ በ2014 ዓ/ም የሌማት ትሩፋት ከመጀመሩ በፊት 917,000 ጫጩት የተሰራጨ ሲሆን በ2015 1.6 ሚለየን በ2016 1.951 ሚለየን ጫጩት፣ በ2017 4 ሚለየን ለማሠራጨት ታቅዶ እስካሁን 927,000 ተሰራጭቷል ።
ዶሮ ከውጭ ሀገር የሚገባ በመሆኑ እጥረት በመከሰቱ ይህን ለማቃለል ከፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገር በሀገር ውስጥ “Grandparent stock” በሀዋሳ ማባዛት በመጀመሩ በቀጣይ ሚያዝያ ማሰራጨት ስለሚጀምር ችግሩ ይፈታል።
በማር ምርት በ2015 ዓ/ም 56,000 ቶን፣ በ2016 ዓ/ም 70,000 ቶን እና በ2017 ዓ/ም 72,000 ቶን ለማምረት ታቅዶ እስካሁን 14.8 ቶን ማምረት ተችሏል።
በዓሣ ምርት የሌማት ትሩፋት ከመጀመሩ በፊት በክልሉ ከ700-800 ቶን ብቻ ይመረት ከነበረበት በ2015 1206 ቶን፣ 2016 ዓ/ም 1600 ቶን፣ በ2017 ዓ/ም 7000 ቶን ታቅዶ በእስካሁኑ አፈጻጸም 2100 ቶን ማድረስ ተችሏል፤ ከ500 በላይ የአረሶ አደር ኩረዎች ለምቶ የዓሣ ጫጩት ገብቷል።
ዘርፉን ለማነቃቃትና የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ለገበያ ማቅረብ እንዲያስችል ከፌደራል ግብርና ሚንስቴር በ7 ሚለየን ብር የዓሣ ማጓጓዣ መኪና ገዝቶ ማቅረቡ፣ በ5 ሚለየን የክልሉ መንግስት የዓሣ ማባዣ ማዕከል በቦንጋ እያስገነባ ይገኛል።
በደውሮ ዞን ሎማ ወረዳ በዓሣ ማስገር ለተደራጁ ወጣቶች በLLSP ፕሮግራም ሶላርና ጀልባ በመቅረቡ በቀን ከ100ኪ.ግ የማይበልጥ ዓሣ ከሚያመርቱበት አሁን በቀን ከ400 እስከ 500 ኪ.ግ ማምረት የተቻለበትና በዋጋም ሆነ በአመጋገብ ዘይቤ በክልሉ ውስጥ ለውጥ መጥቷል ።
በቀይ ስጋ ዘርፍ በማድለብና በማሞከት ክልሉ የሚታወቅበት በመሆኑ በአጭር ጊዜ የተሻለ ምርት ለማቅረብ በመኖ ልማት ላይ መጠነ ሰፊ ስራ ተጀምሯል ።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግና ለማቅረብ የሚወስደውን ጊዜ ለማሳጠር በመኖ ልማት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በፊት በዓመት ከ7 እስከ 8ሺ ሄ/ር ይለማ ከነበረበት በ2016 ዓ/ም 17,000 ሄ/ር ማልማት የተቻለ ሲሆን በ2017 ዓ/ም 18, 500 ሄ/ር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 12,000 ሄ/ር ተሳክቷል ።
የመኖ አቅርቦትን በአካባቢ በማባዛት ከማቅረብ አንጻር በዳውሮ ዞን የመኖ ማባዣ ማዕከል ግንባታ መጀመሩና በካፋ ዞን በዞኑ መንግስት መጀመሩ እንደ አብነት ይጠቀሳሉ።
የሌማት ትሩፋቱ ከመጀመሩ በፊት በክልላችን ከአዲ ስአበባ ሲመጣ የነበረው የምጥን መኖ አቅርቦት አሁን በቦንጋ ዶሮ እርባታ፣ በአባይነሽ ፋርም፣ በቤንች ማጂ ህብረት ስራ ዩኒየን ማከፋፈል መጀመሩ እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ ጉዳይ ነው።
በተጨማርም በምዕራብ ኦሞ ከLLRP ፕሮጀክት ጋር በመሆን የዶሮ ጫጩት ማባዣ ለመትከል ዝግጅት ላይ መሆኑ፤ ከግብርና ሚንስቴር ጋር በመሆን በዳውሮ ዞን የመኖ ማሽን ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ ክልሉ የሌማት ትሩፋትን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አለው።
መ/ኮ፦ ግቡን ለማሳካት በክልሉ መንግስትና በባለድርሻ አካላት የተደረገ ድጋፍ ምን ይመስላል ?
አቶ ታመነ፦ በክልሉ መንግስት ለሌማት ትሩፋት ራሱን የቻለ በጀት ተመድቦ የሚሰራ ባይሆንም ካፒታል በጀትን በመመደብ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት በማካናወን እና በክልሉ የኑሮ ማሻሻያ ላይ የተያዙ በጀቶችን በተዘዋዋሪ በመመደብ በዘላቂነት የታቀደውን ግቡን በተያዘለት ጊዜ ገደብ ለማሳካት እየተሰራ ነው።
የግደር ማባዣ ጣቢያ ባለመኖሩ ከዚህ በፊት ከደቡብ ክልል ካንባታ ጣንባሮ ዞን ይመጣ የነበረውን ችግር ለመቅረፍ በ75 ሚለየን ብር የራንች ግንባታ መጀመሩ፣ በ46 ሚለየን ብር የዶሮ ማባዣዎች ግንባታ፣በ35 ሚለየን ብር በቦንጋ ማዕከል የዓሣ ጫጩት ማባዣ ፕሮጀክት መጀመሩ ፣ በዳውሮ ዞን ታርጫ የመኖ ማባዣና ለችግር ጊዜ ማቆያ በ28 ሚለየን ብር ኘሮጀክቱ መጀመሩ፣ የተሻሻሉ ግደሮችን ለማቅረብ 75 ሚለየን ብር መመደቡ ለአብነት ይጠቀሳሉ ።
በተጨማሪም ከክልሉ በተቀመጠው አቅጣጫ የታችኛው መዋቅሮች በከተሞች ችግሩን ለመቅረፍ 90 ሼድ ከገነቡት መስፈርቱን ያሟሉ 70 ሼዶች በመረከብ በ50 ውስጥ 42,000 የዶሮ ጫጩት መግባቱ፤ 14 ሚለየን ብር ከክልሉ ግብርና ቢሮ ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ፕሮግራም በድጋፍ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፦
በስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ (FSRP) በ8 ሚለየን ብር 23,000 ጫጩት መሠራጨቱ፣ በSLMP ፕሮግራም በሦስት ሚለየን ብር 6000 ጫጩት፣ CALM ፕሮግራም በ3.75 ሚለየን ብር 5200 ጫጩት ድጋፍ ማድረግ ተችሏል ።
መ/ኮ፦ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ በተያዘለት ጊዜ ገደብ በሁሉም አካባቢ ወጥ በሆነ አፈጻጸም ለማሳካት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ታመነ፦ በየደረጃው የሚገኙ የስትሪንግ ኮምቴ የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የግምገማ ስርዓት ያለመጠናከርና ወጥነት ያለመኖር፣ በየመዋቅሩ በተለይ ከተሞች አካባቢ ወጥ የሆነ መዋቅር አለመኖርና የዘርፉ ባለሙያ እጥረት፣ የራሱ የሆነ የስልጠና፣ የድጋፍ፤ የግብዓት ማሟያ በጀት ውስንነት፣ ግብዓት ከሩቅ ስለሚመጣ በሚፈለገው ልክ በጊዜ በሚፈለገው መጠንና ጥራት ለማቅረብ መቸገር ናቸው።
መ/ኮ፦ በቀጣይ ሊሻሻሉ ይገባሉ የሚሏቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
አቶ ታመነ፦ በእንስሳት በተለይ የወተት ላሞች ዝሪያ ማሻሻል ፣ የአካባቢው ልዩ ብራንድ የሆነው የማር ምርት ጥራት እንዳይበላሽ የኬሚካል አጠቃቀም ጥንቃቄ ማድረግ እና በተፈጥሮ አያያዝ ላይ መስራት እና የንብ ዕርባታውን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ ማሸጋገር ፣
በዶሮ እርባታ እያንዳንዱ ቤተሰብ 30 ዶሮ እንዲያረባ ማድረግ ስለሆነ ግቡን ከማሳካት በምጥን መኖ ላይ ትኩረት መስጠትና የመሬት ጥበት ሳያግደው የተንቀሳቃሽ ቤት ቴክኖሎጂን ስርጭትና አጠቃቀም ማስፋት ፣ለአርቢዎች የመሬት አቀርቦት ላይ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ፣ ሁሉም አካባቢ ወደ አንድ ወጥ የሆነ ደረጃ ከማምጣት ከመዋቅር መዋቅር ያለውን ክፍተት በማጥበብ ገበያውን ተመጣጣኝ በማድረግ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል ።
በጌታሁን ግርማ
