Spread the love

የደረሱ የማሽላ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ከብክነት መታደግ እንደሚገባም የክልሉ ግብርና ቢሮ አሳስቧል ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በበልግና በመኸር እንዲሁም በመስኖ ግብርና ስራዎች በሰብል ልማት በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታገል ገብሬ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በዋነኝነት ከሚለሙ ሰብሎች ማሽላ አንዱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታገል በቆላማና አርብቶ አደር አካባቢዎች በስፋት የሚለማና የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ያለው ሰብል ነው ብለዋል ፡፡

ማሽላ ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች የሚከሰተውን የዝናብ ዕጥረትና ድርቅን በመቋቋም ምርት የሚሰጥና በስድስቱም ዞኖች የሚለማ ሰብል መሆኑንም አቶ ታገል ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በማሽላ ሰብል 70 ሺህ ሄክታር ማሳ የተሸፈነ ሲሆንም ከዚህም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ብለዋል ፡፡

አቶ ታገል አያይዘው ወቅቱ ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ አርሶና አርብቶ አደሩ ምርቱ ሳይባክን በወቅቱ እንዲሰበስቡ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በምዕራብ ኦሞ ዞን የማጂ ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተራመድ በቀለ እንደገለጹት በመኸር ግብርና ስራዎች 3 ሺህ 3 መቶ 75 ሄክታር መሬት በማሽላ ሰብል መልማቱን አስረድተዋል ፡፡

ከዚህም ውስጥ 147 ሺህ 416 ኩንታል የማሽላ ምርት እንደሚገኝም አቶ ተራመድ ተናግረዋል ፡፡

በማጂ ወረዳ የአዲካስ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ መኮንን በቱም አካባቢ ባላቸው ማሳ ላይ 2 ጥማድ ተኩል የማሽላ ሰብል ማልማታቸውን ተናግረዋል፡፡

የደረሰውንም ሰብል ምርት ሳይባክን ለመሰብሰብ ከአካባቢው አርሶአደሮች ጋር በመሆን በደቦ እንደሚሰበስቡ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር ኤርሚያስ ከዚህ ቀደም በባህላዊ አስተራረስ በመጠቀማቸው በቂ ምርት አለማግኘታቸውንና በቀጣይም ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ለማልማት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *