




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በምግብና ስርዓተ ምግብ ፕሮግራም ማስጀመሪያ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በክልሉ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በምግብና ስርዓተ ምግብ አተገባበር ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ የነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ከአምስት አመትና ከሁለት አመት በታች ህፃናት የምግብና የስርዓተ ምግብ ልየታ ስራ ከባለፈው የተሻለ አፈፃፀም ቢኖርም የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ርብርብ ልደረግ እንደሚገባም አቶ ኢብራሂም አሳስበዋል።
የምግብና ስርዓተ ምግብ ትግበራ ውጤታማነት ለጤና ዘርፍ ብቻ የሚተው ሳይሆን ሌሎች እንደ ግብርና፣ ትምህርት፣ ሴቶችና ህፃናት፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሴክተሮችም በባለቤትነት ልተገብሩ የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም የቢሮ ኃላፊ አብራርተዋል።
ጤና ተቋማት ዘውትር ክፍት በመሆን የዘርፉን አገለግሎት በተገቢው ተደራሽ ልያደርጉ እንደሚገባቸውም የተገለፀ ሲሆን ከዘርፉ የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነት ጋር ተያይዞ ያለው ማነቆ ልፈታ ይገባል ተብሏል።
በየደረጃው ያሉ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶችን፣ የሀይማኖት ተቋማትን እንዲሁም እድርና ሌሎች ማህበራዊ መሠረቶችን በተገቢው መጠቀም ለምግብና ለስርዓተ ምግብ ፕሮግራም ስኬታማነት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተብራርቷል።
የስልጠና ሰነድ ያቀረቡ የዩኒሴፍ የዘርፉ ባለሙያ አቶ እስራኤል አለማየሁ በበኩላቸው ማህበረሰቡ የሚያመርተውና የሚመገበው ምግብ ለጤና ተስማሚ እንዲሆን ግንዛቤ መፍጠርና ማስተማር ከሁሉም የባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነም ተገልጿል።
የማህበረሰቡን የምግብና የስርዓት ምግብ እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍ ፈጠራን መሠረት ያደረገ ጥናት፣ ትምህርትና ስልጠና፣ ፖልሲ ፣ የማህበረሰብ ተሳትፎና የምርት እድገትን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ተብሏል።
ዩኒሴፍ በክልሉ የምግብና ስርዓተ ምግብ ፕሮግራም በተገቢው ውጤት እንዲያመጣ የሚያደርገውን የአቅም ግንባታና ሌሎች ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
ፕሮግራሙ በክልሉ የምግብና ስርዓተ ምግብ እጥረት ችግር ባለባቸው በዳውሮ ዞን ገና ወረዳ፣ በኮንታ ዞን ኤላ አንቻኖ ወረዳና በምዕራብ ኦሞ ዞን መኤንት ሻሻ ወረዳ ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የኮንታ፣ የዳውሮና የምዕራብ ኦሞ ዞኖች የባለድርሻ አካላት ለፕሮግራሙ ስኬታማነት እንደየአከባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
