ፓርቲው ባለፉት ጊዜያቶች የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን በሪፎርሙ ያሳካቸው ስኬቶች በህዝቡ ዘንድ ባህል ሆነው እንዲቀጥሉ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።

Spread the love

በኮንታ ዞን “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ መድረክ ከዞን፣ ወረዳና ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አመራር አካላት ጋር የምክክር መድረክ መካሄድ ጀምሯል።

መድረኩን የመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ገነት መኩሪያ መድረኩ የብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ዙር ጉባኤ ከተካሄደበት 2014 ዓ.ም ወዲህ ባለፉት ሁለት ዓመት ከግማሽ ጊዜያት ውስጥ በሀገሪቱ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶችና ጉድለቶች በጋራ ተመክሮ ለሁለተኛው ዙር ጉባኤ መነሻ ጉዳዮች የሚያዙበት ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት እንደ ፓርቲና መንግስት የተግባራት ሂደትና ውጤት የሚታይበት በተለይም በንቅናቄ ሲሰሩ የነበሩ ጉዳዮች በህዝቡ ዘንድ ባህል ሆነው እንዲቀጥሉ መስራት እንደሚገባ ያነሱት ወ/ሮ ገነት የብልፅግና ፓርቲ እሳቤ የሆነው የመደመር ፕሮግራሞች ትግበራ በማጠናከር የብልፅግና ጉዞ ማፅናት ይገባናል ብለዋል።

ለውጡ ስኬታማ መሆን የሚችለው ሀሳብን ወደ ተግባር መቀየር የሚችል የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ሲኖር ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ የኢትዮጵያን አንድነት በማፅናት ላይ መስራት ያሻልም ብለዋል።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው የብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ማስመዝገቡን በመጠቆም በእኚህና ጉድለቶች ላይ፣ በፓርቲው መተዳደሪያ እና በስነምግባርና ኢንስፔክሽን በኩል በታዩ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ የሚያዝበትና ጉድለቶች የሚሞሉበት መድረክ ስለመዘጋጀቱ ገልፀዋል።

መድረኩ በነገው ዕለትም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን ወ/ሮ ገነት ለምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ለውይይት መነሻ የተዘጋጀውን ሰነድ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ዘገባው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *