በፓርቲው መሪነት የመጡ ለውጦችን ለማስቀጠልና የቀጣይ ህልሞችን ለማሳካት መላው አባልና ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ።

Spread the love

በብልፅግና ፓርቲ የኮንታ ዞን ቅ/ጽ/ቤት ዞናዊ የአባላት ቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በኮንፈረንሱ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪና ብልፅግና ፓ/ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ገዝሙ ፓርቲያችን ብልፅግና ሀገራችን ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በገባችበትና በፈተና ውስጥ ሆና የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ገንፍሎ በመውጣቱ የተወለደ ፓርቲ ነው ብለዋል።

በመላው ኢትዮጵያ ከ16 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉትና በሀገሪቱ ታሪክ በአጭር ጊዜ ራሱን አደራጅቶ ሀገሪቱን ከውስብስብ ችግሮች ለመታደግ እየሰራ የሚገኝ ጠንካራ ፓርቲ ነው ያሉት አቶ ገዛኸኝ በፓርቲው መሪነት በሀገሪቱ ብሎም በኮንታ ዞን ሰፊ ትሩፋቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።

የኮንታን ዞን የመዋቅር ጥያቄ ከመመለስ ጀምሮ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ዘርፎች ውጤታማ የሆነው በፓርቲው መሪነት ነው ያሉት ዋና የመንግስት ተጠሪው ለአብነትም በትምህርት፣በመንገድ፣ በጤና፣ በግብርና በመሠረተ ልማትና ወዘተ. ዘርፎች ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን አብራርተዋል።

ብልፅግና ፓርቲ እንደሀገር ብሎም እንደዞን ያስመዘገባቸው ድሎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የቀጣይ ህልም የሆነውን በሁሉ አቀፍ ዘርፎች በአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው እንቅሰቃሴ በማጠናከር መላው አባልና ማህበረሰብን የሚያከፋፍሉና የሚያጠለሹ ተግባራትን በመከላከል የፓርቲው ቅቡልነት የበለጠ እንዲጎላ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

በፓርቲው መሪነት ባለፉት ሁለት ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ ብሎም በዞኑ የመጡ ዋና ዋና ትሩፋቶችንና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ላይ “ከቃል ወደ ባህል” በሚል መሪ ቃል የግንዛቤ ሰነድ ያቀረቡት የዞኑ ረዳት የመንግስት ተጠሪና ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባሻ በላቸው ፓርቲው በብሶት ከተወለደበት ወዲህ በሀገሪቱ ብሎም በዞኑ ታሪካዊ የሆኑ ድሎች ተመዝግበዋል ብለዋል።

እንደኮንታ ዞን የቱሪዝምና የማዕድን ዘርፍ መነቃቃት፣ በትምህርት ዘርፍ የኢሞታ ልዩ ት/ቤት ግንባታና የመማሪያ መጽሐፍት ህትመት፣ የመንገድና የህንፃዎች ግንባታ፣ የግብርናና ሰው ተኮር ተግባራት ከብዙ በጥቂቱ የሚገለፁ ናቸው ያሉት አቶ ባሻ ተግባራቱ ቀጣይነት እንዲኖራቸው የሁሉም ማህበረሰብ ድርሻ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የዞኑ ረዳት የመንግሥት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ እንግዳወርቅ ዶኖቾ በበኩላቸው ፓርቲው ሰው ተኮር ስራዎችን ለማገዝ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየቱን በመጠቆም ፕሮጀክት ጀምሮ መጨረስን ባህል ያደረገ፣ የአረንጓዴ አሻራ ቅቡልነት ፤አረጋውያንን የመደገፍ ፤የማዕድ ማጋራት ሥራዎች፣ የሌማት ትሩፋት እና ሌሎች ተግባራት ተግባራዊ ማድረጉ ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸው ገልፀዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በብልፅግና ፓርቲ መሪነት የመጡ ለውጦች እጅግ አበረታች መሆናቸውን ተናግረው ይህም በአመራር ቁርጠኛ አፈፃፀምና የህብረተሰብ ተሳትፎ ማደግ የመጣ መሆኑን በመግለፅ ይህንን ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አንስተዋል።

በኮንፈረንሱ የፓርቲ የስነምግባርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ኮሚቴ እና የክልል ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ምርጫ ተካሂዷል።

በመጨረሻም ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ ተነቦ ኮንፈረንሱ የተጠቃለለ ሲሆን በኮንፈረንሱ የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ፣ የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ገዝሙን ጨምሮ አጠቃላይ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች የተወከሉ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘገባው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *