
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ የሆነው የከተራና የጥምቀት በዓል እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የቆየ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ያሏት ታሪካዊት ሀገር ነች ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።
የከተራና የጥምቀት በዓላት የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የአንድነት ሁነት በመሆኑ ቅርስነቱ በዩኔስኮ መመዝገቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴት መሆኑንም ተናግረዋል ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 በድምቀት የሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል አሰባሳቢና ለቱሪዝም ትልቅ ፋይዳ ያለው እሴት ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን የሐይማኖቱ ተከታዮች በመንፈሳዊ ዝማሬዎች ታቦታቱን አጅበው ወደ ጥምቀተ ባህር በመውረድ በድምቀት የሚያከብሩት በዓል ነው ብለዋል።
የክልላችን የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ በፍጹም የእምነቱ አስተምህሮ የሚያዘውን ሰላምን በማስተማር ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ።
የከተራና የጥምቀት በዓላት ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የሀገርን ገጽታ በእጅጉ ከሚገነቡት ውስጥ አንዱ በመሆኑ ልንጠብቀውና ልንንከባከበውነቀ ልናለማዉ ይገባል ብለዋል።
በዓሉን ስናከብር በዮርዳኖስ ወንዝ በክርስቶስ ኢየሱስ የጥምቀት ቀን በመጥምቁ ዮሐንስና በኢየሱስ መካከል እንደታየው የመከባበር የመቻቻልና የመደናነቅ እሴቱን ዳግም እየገነባን ሊሆን ይገባል።
በበዓሉ ወቅት ያለንን በመካፈልና አብሮ በማክበር የዕምነቱ ተከታዮች ለተቸገሩት በማካፈልና በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እስኪጠናከር ሁሉም በጋራ ተባብረው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በዓሉ የሰላም ፣የፍቅር፣የአንድነትና የመተሳሰብ እንዲሆንም ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ተመኝተዋል።
