የከተሞች ፈርጅ ለውጥ ለከተሞች እድገትና ለአገለግሎት አሰጣጥ መሻሻል ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለጸ

Spread the love

የክልሉ መንግስት ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመሰጠት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ተብራርቷል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዳውሮ ዞን የታርጫ ከተማ ከፈርጅ ሶስት ወደ ፈርጅ ሁለት ያደገበት ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሂዷል።

በመርሃግብሩ የተገኙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል የክልሉ መንግስት ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመሰጠት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የታርጫ ከተማ የደረጃ ለውጥ የቆየ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን ያነሱት ኢንጂነር የማታለም የክልሉ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ለጥያቄው ምላሽ መስጠት መቻሉንም አብራርተዋል።

ኢንጂነር የማታለም አክለውም በፍጥነት እያደገ ያለውን ከፍተኛ የከተማ ህዝብ ቁጥርን የሚሸከሙ ከተሞችን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ለከተማው ነዋሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው ዞኑ በለውጥ መንግስት በርካታ ጥቅሞችን እያገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

የለማና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከሞችን ለነዋሪዎችና ለእንግዶች ለመፍጠር የሁሉም የባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ ዳዊት።

በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመሩ የከተማ ውበትና የኮሪደር ልማት ስራዎች በዞኑ በሁሉም አከባቢ ተግባራዊ እንዲደረግ የተጀመሩ ርብርቦች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አንስተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ አገለግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ንግድ ቤቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ለከተማዋ ለውጥ ያላቸውን ሚና በአግባቡ ልወጡ ይገባልም ተብሏል።

ለከተማዋ የፈርጅ ለውጥ የነዋሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የገለፁ የታርጫ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳዊት ወንድሙ ለከተማዋ የፈርጅ ለውጥ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን በሙሉ አመሰግነዋል።

አቶ ዳዊት አክለውም ከተማዋ የፈርጅ ለውጥ ማድረጓ ለከተማዋ በዓለም ባንክ የመታቀፍ እድል ከማስገኘትም ባለፈ ለነዋሪዎች የተሻለ አገለግሎት ለመስጠት ያስችላልም ብለዋል።

ከ15 ሺ በላይ ነዋሪዎች ይዛ በ1993 የዳውሮ ዞን ዋና ከተማ የሆነች የታርጫ ከተማ በአሁኑ ሰዓት ከ75 ሺ በላይ ነዋሪዎችን በውስጧ ይዛ ከፈርጅ ሶስት ወደ ፈርጅ ሁለት አድጋለች።

ለከተማው ሁለንተናዊ ብልፅግናና እድገት ነዋሪዎች በገንዘብ፣ በሀሳብና በጉልበት የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሃግብሩ የተገኙ የባለድርሻ አካላት በተማዋ የፈርጅ ለውጥ መደስታቸውን ገልፀው በቀጣይ በከተማዋ ለሚደረጉ የልማት ስራዎች ሚናቸውን በብቃት እንደሚወጡ ተናግረዋል ሲል ደሬቴድ ዋካ ቅርንጫፍ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *