ከ742 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በቦንጋ ከተማ ግንባታ እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽን የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከል ግንባታ 98 ከመቶ መድረሱ ተገለጸ።

Spread the love

ግብርናን ለማዘመን መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

ከነዚህ የመንግሥት ጥረቶች አንዱ የግብርና ግብዓቶችን በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ ለአምራቾች ተደራሽ የማድረግ ተግባር ሲሆን በደቡብ ምዕራብ ቀጠና ይህንኑን ተግባር የሚያሳልጠው የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ በ2014 በጀት ዓመት ማገባደጃ ወደ ግንባታ መግባቱን ነው የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አማካሪ አቶ ካሳሁን ከበደ የገለጹት።

ኮርፖሬሽኑ ባለፋት ዘጠኝ ዓመታት የግብርና ዘርፉን በተሻለ መልኩ እያደገፈ እንደሚገኝ የጠቆሙት አማካሪው አጠቃላይ ከ7.5 ቢሊዮን ብር በላይ የኾነ ካፒታል የሚያንቀሳቀስ በሀገሪቱ ብቸኛው የመንግሥት የግብርና ግብዓት አቅራቢ የልማት ድርጅቱ መሆኑን አንስተዋል።

በደቡብ ምዕራብ ቀጠና ተደራሽነቱን በማስፋት ለአምራቾች የተሟላ የግብርና ግብዓትና የእርሻ ቴክኖሎጂ መሳሪያ ለማቅረብ በማቀድ በ742 ሚሊየን ብር ግንባታው እየተገባደደ ያለው የተቀናጀ የኮርፖሬሽኑ ምርት ማዕከል አሁን ላይ ግንባታው 98 ከመቶ መድረሱን ነው አቶ ካሳሁን የገለጹት።

እንደሀገር የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በቦንጋ ማዕከል በቀጠናው የጥራት ደረጃው የተሻሻሉ ምርጥ ዘር በማምራት ለማቅረብ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ካሳሁን አሁን ከፊል በተጠናቀቀው ህንጻ በኮርፖሬሽኑ እርሻ በአከባቢው የተመረተውን ምርጥ ዘር ማከማቸት መቻሉን ገልጸዋል።

የማዕከሉ ግንባታ በሁለት ሎት ተከፍሎ እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት አቶ ካሳሁን ግንባታው በውስጥ የተለያየ መጠን ያላቸው የእህል ማከማቻ መጋዘኖች፣ ማበጠሪያ ማሽን ክፍሎችና የተለያዩ የኬሚካል ማከማቻ ፣ የአስተዳደር ሠራተኛ ቢሮ እንዲሁም የእርሻ ማሽነሪዎች ማከማቻና መስጫ ሼዶች በውስጡ ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘርና የደን ውጤቶች ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘነበ ወ/ሰንበት በበኩላቸው ማዕከሉ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ በቀጠናው ተደራሽ በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ የሰብል ዘርን በተለያዩ መንገድ በመሰብሰብ በማዘጋጀትና ደረጃ በማውጣት ለእርሶና ከፍል አርሶአደሮች እንደሚያቀርብ የገለጹት ስራ አስፈጻሚው እንደሀገር በ2016/17 ምርት ዘመን 465 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የተለያዩ የሰብል ዘር በማባዛት ለአምራቾች ለማቅረብ በ25 ቅርንጫፎቹ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በማዕከሉ ግንባታ ውስጥ የማበጠሪያ ማሽን በመትከል ላይ የሚገኙት አቶ ሳይ በበኩላቸው የማሽን ተከላው 95 ከመቶ መድረሱን በመግለጽ በቀጣይ ቅርብ ቀናት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *