በሕገ-ወጥ ድርጊት በሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፦አገልግሎቱ

Spread the love

በሕገ-ወጥ ድርጊት በሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ በሰጠው መግለጫ÷ የፋይናንስ ወንጀሎች በሀገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዘርፈ ብዙ እና ከፍተኛ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በመሆኑ ኢትዮጵያ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ህጎችን አውጥታ በመተግባር እንደምትገኝም አስገንዝቧል፡፡

ለአብነትም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 እየተተገበረ መሆኑ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀድሞ በተለያዩ ህጎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ የህግ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ ራሱን የቻለ የንብረት ማስመለስ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁን አስታውሷል፡፡

የንብረት ማስመለስ አዋጁም ሆነ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጠጠር የወጣው አዋጅ ዓላማ የፋይናንስ ወንጀሎች አትራፊ አለመሆናቸውን በማረጋገጥ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ሁሉን አቀፍ አደጋ መግታት ነው ብሏል፡፡

በሌላ በኩል ለጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም ነው ያስረዳው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ግለሰቦች የወጡ ህጎችን ለማደናገሪያነት በመጠቀም እንዲሁም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና የሌሎች የፀጥታ አካላትን ስም በመጥቀስ በማጭበርበር እና በማስፈራራት በህገ-ወጥ ድርጊት ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ክትትል በማድረግ በተደራጀ አግባብ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ውስጥ 3 ግለሰቦች ዓርብ ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

ሌሎችንም በቁጥጥር ስራ ለማዋል ከህግ አስከባሪ አካላት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

አገልግሎቱ ከራሱ ምንጮችና ከጥቆማ በሚደርሱት መረጃዎች መሰረት የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ እየሰራ ይገኛል ብሏል።

በርካታ ጉዳዮችም በህግ ተይዘው ይገኛሉ ያለው አገልግሎቱ÷ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አገልግሎቱ የሚወስዷቸውን ርምጃዎች የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።

ህብረተሰቡም ማጭበርበርን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ወንጀል በመፈጸም የሚገኝን ገንዘብ ህጋዊ ለማስመሰል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሲመለከት በ9796 ነፃ ስልክ ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በመደወል ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል ሲል ኤፍ ኤም ሲ ዘግቧል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *