በክልሉ በመሠረተ ልማት እና በማህበራዊ ዘርፎች የህዝብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያው ጉባኤው አቅጣጫ መነሻ በክልሉ በመሠረተ ልማትና ማህበራዊ ዘርፎች በተሰሩ ሥራዎችና በተገኙ ውጤቶች ላይ ከሚዲያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቆይታቸውም፤ባለፉት ሶስት ዓመታት በመሠረተ-ልማት እና በማህበራዊ ዘርፎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሥራዎች መከናወናቸውና በዚህም እምርታዊ ውጤቶች መመዘገባቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ሰፊና ትልቁ ተግዳሮት የሆነው የመንገድና የድልድይ መሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በፌደራል መንግስት መንገድ ልማት ፈንድ ጨምሮ ፣በክልሉ አቅምና በማህበረሰብ ተሳትፎ 1.3 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ባለፉት ሶስት ዓመታት 1 ሺህ ኪ/ሜ የገጠር ለገጠር አዲስ መንገድ ከፈታና ነባር መንገዶች ጥገና ሥራዎች መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት የከተማ ኮሪደር ልማት ዘግይቶ የተጀመረ ቢሆንም በዋና ዋና ከተሞች ሰፋፊ የከተማ ኮሪደር ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን በመጠቆም የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማና መዝናኛ ቦታዎችን ለማነቃቃት ፣ የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የከተማ መኖሪያ ቤቶች ደረጃቸውን ከማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ማህበረሰቡ በኮሪደር ልማት ሥራ የሌሎች አከባቢ ልምድ በመቀመር በገንዘብ፣ጉልበትና በሌሎች ጉዳዮች ተባባሪ በመሆን ለስራው ለሚያደርጉት ትብብር አመስግነው ስራው እስኪጠናቀቅ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

በፌደራል መንግስት በጀት ድጋፍ እየተሰራ የሚገኘው የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ በተሻለ ደረጃ እየተከናወነ መሆኑንና ከግል ባለሀብት ጋር በመቀናጀት የሚለማው ቦንጋ ቀላል አውሮፕላን ማረፊያ ስራው የተጀመረ በመሆኑ ፍጥነት በመጨመር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

በቦንጋ ከተማ በፌደራል ግብርና ኮርፖሬሽን የሚገነባው የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ማሽነሪ አቅርቦት ማዕከል በውስጡ የምርጥ ዘር ማቀነባበሪያ፣የማሽን አቅርቦት፣ማበጠሪያ፣የቴክኒክ ስልጠና ማዕከላትና ማከማቻ መጋዘን የያዘ ሲሆን ግንባታውም 98 በመቶ እንደደረሰም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

የቱሪዝም መዳረሻዎች ”’ገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀከት” አካል የጨበራ ዳና እና ሃላላ ኬላ ኢኮ-ሎጅ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው የአከባቢውን ገጽታ በመቀየር የቱሪዝም ዘርፍ እያነቃቃ መሆኑንና ”ገበታ ለትውልድ” የደንቢ ሀይቅ ኢኮ- ሎጅ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ እንዳለም ጠቁመዋል።

በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽ/ቤት የተገነባው የቦንጋ ከተማ ዱቀት ማቀነባበሪያ እና ዳቦ ፋብሪካ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት 270 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን አቅርቦት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ 4መቶ ሺህ ማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ያሉት ሲሆን የክልሉ የውሃ ሽፋን ቀደም ሲል ከነበረው ከ32.7 % ወደ 43.7% ማሳደግ መቻሉንና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችም በሂደት ላይ እንዳሉት አንስተዋል ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ”ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ” የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ከተወሰደው እርምጃዎች የትምህርት ቤቶች ደረጃ ከማሻሻል አኳያ ባለፈው አንድ ዓመት 416 ሚሊዮን ብር ከማህበረሰቡ በማሰባሰብ ከ1ሺህ በላይ ት/ቤቶች አዲስ የመማሪያ ከፍሎችን መገንባት፣ጥገና እና የውስጥ ቁሳቁስ ማሟላት ተችሏል ብለዋል።

ከ160 ሚሊዮን በላይ ብር በማህበረሰብ ተሳትፎ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት መታተሙንም ገልጸው በተያዘው ዓመት በሁሉም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቅድመ አንደኛ ደረጃ የመዋለ-ህጻናት መማሪያ ክፍሎች እንዲሁም በሁሉም ወረዳዎች ሞዴል የቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ለማዘጋጀት በማህበረሰብ ተሳትፎ መረሐ-ግብሩ ተጀምሯል ነው ያሉት።

የጤና መሠረተ ልማት ለማስፋት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ጤና ጣቢያዎች፣ የደም ባንክና ሌሎችን ጨምሮ 15 ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቆ ወደ ልማት እንዲገቡ መደረጉንና ቀሪ 18 ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።

በሽታ ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር የወባ በሽታ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር በጋር በመሆን በተቀናጀ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች እየመጡ ቢሆኑም ዘርፉ አሁንም ትኩረት እንደሚፈልግ ነው ዶክተር እንጂነሩ የገለጹት።

ሕገወጥ የህክምና መድሃኒት ዝውውርና ግብይት መከላከል፣ ማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ማስፋት እንዲሁም የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ደረጃቸውን ማስጠበቅ ጎን ለጎን የሚሰሩ ጉዳዮች በመሆናቸው ማጠናከር ይጠበቅብናል ።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንሼቲቭ 2ሺ 4መቶ አረጋውያን እና የአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ በማህበረሰብ ተሳትፎ ግንባታ የተከናወነ ሲሆን በገንዘብ ሲተመን ከ210 ሚሊዮን በላይ ብር እንደሆነና በወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማዕድ በማጋራት ቀላል የማይባሉ ሥራዎች ተሠርቷል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በመሠረተ-ልማት እና በማህበራዊ ዘርፎች በማህበረሰብ ተሳትፎ ለቀጣይ ጊዜያት ትልቅ መደላድል የፈጠረና መሠረት የጣሉ ተግባራት የተፈጸመበት በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት፣ ትምህርት፣ጤና፣ የመንገድ መሠረተ ልማት እና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች ቀጣይ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸውም ብለዋል በቆይታቸው።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *