ከማምረት የሚሻገር ዕድል ይዘው የመጡ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል

Spread the love

ሪፖርታዥ

ከማምረት የሚሻገር ዕድል ይዘው የመጡ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል

የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ከሚያመላክቱ ጉዳዮች አንዱ የዜጎች አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነት መረጋገጥ መቻሉ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በብዙ ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚስተዋለው የመቀንጨር ችግር ከኢትዮጵያ እንዲጠፋ ዘንድ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንዳለ ማወቅ ተችላሏል።

ከእነዚህ የመፍትሔ አቅጣጫዎች አንዱ ዜጎች በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን በቀላሉ በጓሯቸው እያመረቱ መጠቀም እንዲችሉ የሚያነሳሳ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ከተዋወቀ በኃላ ከተለያዩ አጋር አካላት እና ፕሮጀክቶች ጋር በመተባበር በክልላችንም እተሰራ ይገኛል።

ይሁን እንጂ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች አቅርቦት ችግር እንዳለ ሆኖ የምርቶቹ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመሄዱ ዜጎች በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን ከመጠቀም እየተቆጠቡ ይኸዳሉ፤ ለዚሁ ችግር ደግሞ ቀዳሚው መንስኤ የመኖ እጥረትና ዋጋ መናር ነው።

እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት ክልሉ በወሰደው አወንታዊ እርምጃ ዞኖችን በማስተባበርና ለእያንዳንዳቸው ግማሽ ያህል የበጀት ድጋፍ በማድረግ በ27.5 ሚልዮን ብር ወጪ 6 የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ግዢ ተፈጽመው ወደ ማምረት ለማስገባት የክሂሎት ስልጠና መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የእንስሳትና ዓሳ ልምት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ ተናግረዋል።

አንድ ዞን ቢያንስ አንድ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ቢኖረው ለአካባቢው መኖን ተደራሽ እንዲያደርግ ያግዛል ያሉት አቶ ታመነ: የምርት ሂደቱ በጥራት እንዲሻገር አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል ለማድረግም ያመቻል ብሏል።

በዚሁ የአንድ ማሽን ለአንድ ዞን መርህ ለ6ቱ ዞኖች የተገዛው ማሽን መኖ ከማቀነባበር ባሻገር ስራ አጥ ከሆኑት ወጣቶች 59 ያህሉ ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው ወደ ስራ ሲገቡ የሚያግዛቸውን ስልጠና መውሰደሰቸውን ተናግረዋል።

ለእነዚህ ማሽኖች የሚሆኑ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የሚገኙባቸው ግብዓቶች(ሰብሎች) ላይ በቂ ግንዛቤ ቀስመው አቀማመርና አቀነባበር ላይ የኪሂሎት ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች የተሰጣቸው ኃላፊነት ከማትረፍ የሚሻገር የሀገር አደራ መሆኑን አውቀው በኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

ስልጠናው በንድፈ ሀሳብና በተግባር መሰጠቱን ያወሱት አቶ ታመነ: እነዚህ ማሽኖች በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት ከገቡ መንግስት በየደረጃ ያስጀመራቸው የዶሮ፣ የወተት ላሞችና የስጋ መንደሮችና አርቢ ማህበራት ቀጣይነትና ምርታማነት ይረጋገጣል ብለዋል።

ከክልል እስከ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ድረስ ለዚሁ ተግባር መሳለጥ ቅንጅታዊ አሠራር መዘርጋቱን ያወሱት አቶ ታመነ: ለማሽኖች መስሪያ ምቹ ቦታ፣ ሼዶችና መጋዝኖች፣ ለዚሁ ዓላማ የተለዩ የኃይል አቅርቦት ትራንስፎርመር ከመመቻቸቱ በተጨማሪ ለግብዓቶችና መሰል ወጪዎች የሚሆን የብድር አቅርቦት እየተመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል።

የመኖ ማቀነባበር ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ዘመኑ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ራሳቸውን እንዲያበቁና ከዚህ ቀደም በነበሩት ምርቶች ላይ እሴት እየጨመሩ ገበያው ላይ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ከመኖ ዝግጅት ጎን ለጎን በሌማት ትሩፋት ስራዎች ለተሰማሩ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮችና ማህበራት መነሻ የሚሆን የዶሮ ጫጩት ከቦንጋ ዶሮ እርባታ ማዕከል ጋር በመሆን ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ እናቀርባለን ብለው: የወቅቱ ሰልጣኞችም ለእንቁላል ጣይና ለስጋ ዶሮ የሚሆን መኖ በስፋት ለማቅረብ ከወዲሁ እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

ክልሉ የዶሮ እርባታን በሌማት ትሩፋት ከማስተሳሰር ባለፈ በወተት ላሞች እርባታ የተሻለ ልምድና ሪኮርድ ካላቸው የግል ፋርሞች የተሞክሮ ቅመራና ትስስር በመፍጠር ዜጎች የእንስሳት ተዋጽኦ ማግኘት እንዲችሉ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በወቅቱ ስልጠና የሰጡት የግብርና ሚኒስተር ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበበሰ ዙሪያ ብቻ መሠረት ያደረጉ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ወደ ክልሎች እስኪደርሱ የሚያስወጡትን የትራንስፖርት ወጪ ለመቀነስ ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ የማሽኔሪና ክሂሎት ስራን የማሸጋገር ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በሀገር ደረጃ 82 የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች መኖራቸውን ያወሱት አሠልጣኞች: መንግስት አሁን ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ወደ ክልሎች በማስፋፋት 214 ማድረሱ በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶችን በእጅጉ የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ እየሰራ ያለው ስራ በኢትዮዽያ ደረጃ በመቀንጨር ችግር ውስጥ ያሉ 39% ዜጎችን መታደግ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ታመነ: በመኖ እጥረት ሳቢያ ዋጋው እየናረ ያለውን የእንስሳት ተዋጽኦ ገበያ በማረጋጋት ዜጎች ቢያንስ ከእቁላሌ፣ ወተት፣ ስጋና ዓሳ አማካይ ምግብ እያገኙ አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነቱ የተረጋጠ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቀርበዋል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *