




በኢትዮጵያ የኖርዌይ እና የዴንማርክ አምባሳደሮች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኘውንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቅርስ ጥበቃ UNESCO የተመዘገበውን የከፋ ጥብቅ ደን እንዲሁም በደኑ አከባቢ ያለውን የአሳታፊ ደን ማህበር እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
አምባሳደሮቹ በጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ድጋፍ በREDD+ እና CRLF ፕሮግራም በደን ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር መርሀግብር የተሰሩ የደን ጥበቃና ልማት ፣ የኑሮ ማሻሻያ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን በመግለጽ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በጉብኝቱ አጠቃላይ በፕሮግራሞቹ በተሰሩ ዝርዝር ተግባራት ላይ ገለጻ የሰጡት የክልሉ የደንና አከባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አስራት ገ/ማርያም (ዶ/ር) በሁለቱ መንግሥታት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በክልሉ በደንና አከባቢ ጥበቃ የአየር ንብት ለውጥ እንዲሁም ኑሯቸውን በደን ጥገኛ ላደረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች በኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን በመግለጽ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ከጉብኝቱ መልስ በአጠቃላይ የREDD+ ፕሮግራም ዝርዝር አፈጻጸሞች ዙሪያ ገለጻ የሰጡት በክልሉ ደንና አከባቢ ጥበቃ አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም አስተባባሪ የርቾ ብርሃኑ (ዶ/ር) ፕሮግራሙ በደን ተኮር የኑሮ ማሻሻያ መርሀግብር የታቀፉ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አብራርተዋል።
የሁለቱም ሀገራት አምባሳደሮች ፕሮጀክቶች በመደገፍ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸው አበረታች መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው በክልሉ በደን ልማትና ጥበቃ የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጉብኝቱ በሁለቱ መንግሥታት ድጋፍ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ውጤት በማየት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ዕድል የሚፈጠር መሆኑን የገለጹት የርቾ (ዶ/ር) በቀጣይ ቀናት በሌሎች በፕሮግራሙ በሚደገፉ ወረዳዎች የተሰሩ ተግባራት ምልከታ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በጉብኝቱ የኖርዌይ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ቆንስላ ኃላፊ ወ/ሮ ሊቬ ጃክብ፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ሞቱማ ቶሌራ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
