በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በክልላችን በርካታ ውጤቶች ማስመዝገብ ችለናል፦ አቶ ማስረሻ በላቸው

Spread the love

“ኢንዳስትሪ ከመንደር ወደ ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢኖቬሽን ቢሮ በ 3-2-1 የገጠር ኢንደስትሪላይዜሽን ተነሳሽነት ላይ ከክልል ስትሪንግ ኮሚቴዎች ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ሰነድ ያቀረቡት የኢንዱስትሪ ሚንስትር የኢትዮጵያ ታምርት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ታደሰ አስማራ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸው በየዓመቱ በዘርፉ ያሉ የአሰራር ስርዓቶችን ቀልጣፋ በማድረግ ምርትና ምርታማነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በክልላችን በርካታ ውጤቶች ማስመዝገብ ችለናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ መቆየቱን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም እንደሀገር ስራ ያቆሙ ፋብርካዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዘርፍ ላይ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ አብሮ መስራት እንደሚጠበቅ የገለፁት አቶ ማስረሻ ይህ ተግባር በክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴና በአንድ ተቋም ብቻ የሚመራ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ የሌማት ቱሩፋቶች ለኢንዱስትሪ ልማት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረው በኢንዱስትሪ ልማት ኢንሼትቪ በተቀመጠው መሠረት በክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህ ተግባር በተያዘው ዓመትም ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን እንደ ክልል ባሉን የዞን መዋቅሮች ለመተግበር እቅድ ተይዞ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ግዛው ጠቁመዋል፡፡

የኢፌዴሪ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ምልኬሳ ጃጋማ በበኩላቸው ክልሉ የባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጥሩ አፈፃፀም የታየበት መሆኑንና የ2017በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዝግጅት ላይ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

የማሽኔሪ እና ኢክዩፕመንት አቅርቦት ከውጪ ከማስገባት ይልቅ በሀገር ውስጥ አምርቶ ለመጠቀም በሀገር ደረጃ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ያለ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው የአምራች ኢንዱስትሪ ልዩ ካውንስልንግ በመቋቋም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፋታ የሱፍ በበኩላቸው በክልሉ ባለው ሀብት ላይ ዕሴት በመጨመር የተሻለ ዋጋ መውጣት በሚችሉበት መልክ ማምረት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚታዩ ማናቆችን ለመፍታት በአመለካከት ላይ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ለዘርፉ ተግባር የተለያዩ ምቹ የሆኑ አመራጮችን እያመቻቹ መሄድ ይገባል ብለዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *