የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ማገዝና መደገፍ የቀጣናውን ሰላም የማጽናት ስራ ነው – አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ

Spread the love

የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ማገዝና መደገፍ የቀጣናውን ሰላም የማጽናት ስራ መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለጹ።

የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፍረንስ “የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ በአፍሪካ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች ስለመሆኑ አንስተው በጥረቷ ልክ እገዛና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካሳየው ቁርጠኝነት ባሻገር በሽግግር ፍትህ ዘላቂ ፍትህና ሰላምን ለማረጋገጥ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ ወደ ተግባር መግባቱንም አድንቀዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረትም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ገቢራዊ እንዲሆን ከአንድ ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም ለምታደርገው ጥረት የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ውስብስብ ፈተናዎች የተባበረ ጥረትን የሚጠይቁ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ማገዝና መደገፍ የቀጣናውን ሰላም የማጽናት ስራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት ሃላፊና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ(ዶ/ር)፤ ኮንፍረንሱ በውቧ አዲስ አበባ መዘጋጀቱ የተለየ የደስታ ስሜት ፈጥሮልኛል ብለዋል።

የሰላም ኮንፍረንሱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራትና ለአህጉሪቱ ጭምር ወሳኝ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የዓለምን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የአፍሪካን ሰላም መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህ ደግሞ በጋራ ተባብሮ መስራት ይገባል ብለዋል።

የሰላም ጉዳይ የሁሉንም የጋራ ጥረትና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል ነው ያሉት ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *