ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የዴንማርክ እና የኖርዌይ አምባሳደሮችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የዴንማርክ እና የኖርዌይ አምባሳደሮችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አምባሳደሮቹ በክልሉ በሁለቱ መንግሥታት ድጋፍ በደንና አከባቢ ጥበቃ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ለመመልከት እንዲሁም በቀጣይ ፕሮግራሞችን ማስቀጠል በሚቻልበት አግባብ ከክልሉ መንግሥት ጋር ምክክር ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

የክልሉ አብዛኛው ማህበረሰብ ኑሮው በደን ጥገኛ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የደን ጥበቃና አያያዝ ለማሻሻል እንዲሁም ከደኑ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የዴንማርክ እና የኖርዌይ መንግሥታት በREED+ እና በCRFL ፕሮግራሞች በኩል እያደረገ ሌላው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በፕሮግራሞቹ ድጋፍ በደን አከባቢ የሚኖሩ ማህበረሰብ የኑሮ ማሻሻያ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ በቡናና ቅመማ ቅመም ልማት፣ በከብት እርባታ እንዲሁም በማር ምርት ማህበረሰቡ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ይሁን እንጅ ከጥብቅ ደኑ የካርበን ሽያጭ በቀጥታ ተጠቃሚ የመሆን ጉዳይ ምላሽ ባለማግኘቱ ቅሬታ የፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኖርዌይ መንግሥት ካለፋት ረዥም ዓመታት ጀምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በደን ጥበቃና የአየር ንብረት መስክ በትብብር እየሰራ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ስቲያን ክርስቲያንስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በደን ጥበቃና አያያዝ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በደኑ አከባቢ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ኑሮ ለማሻሻል በቀጣይ ከካርበን ሽያጩ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ በክልሉ ያለው የደን ጥበቃና አያያዝ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የዴንማርክ አምባሳደር ሱነ ክሮግስትረፍ በበኩላቸው የተጀመረውን የድጋፍ ማዕቀፍ በማጠናከር በቀጣይ አዳዲስ ድጋፎችን በመዘርጋት የደን ሰክተሩን ለመደገፍ መንግስታቸው ቁርጠኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከካርበን ሽያጭ ኑሮአቸውን በደን ያደረጉ የማህበረሰቡ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ሞቱማ ቶሌራ (ዶ/ር) እስከ ቀጣዮቹ የፈረንጆች 2026 ኢትዮጵያን ከካርበን ሽያጭ የ75 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተጠቃሚ ከኖርዌይ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ሞቱማ ቶሌራ (ዶ/ር) አክለው የገንዘብ ድጋፉ የተጠቃሚ ማህበረሰቦች ውጤትን መነሻ በማድረግ የሚሰጥ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

አምባሳደሮቹ በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በደን ጥበቃና አያያዝ በሁለቱ መንግሥታት ድጋፍ እየተተገበረ ያለውን ተግባራት ተዘዋውረው እንደሚገኙ የተገለፀ ስሆን እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናከረው ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

በልዑኩ የኖርዌይ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ቆንስላ ኃላፊ ወ/ሮ ሊቬ ጃክብን ጨምሮ ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *