“እኛ የምንሸነፈው በነፍሳችን ልናጸናት በቆምንላት ኢትዮጵያችን ፍቅር ብቻ ነው”
የምንወጣ የምንወርደው፣የነፍስ ዋጋ የምንከፍለው፣ የትኛውንም ፈተና የምንጋፈጠው ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ ነው።
አዕምሮውን በመንደር አጥብቦ፣በዕውቀት ሳይሆን በስሜት ልቡን ያሳበጠ፣የስህተቱ ምንጭ የሴረኞች “የጨፍን ላሞኝህ” ሀሳዊ ትርክት መሆኑ በደንብ ይገባናል።በሙያዊ ዲሲፕሊን በሰከነና ጥበብ በተሞላበት የግዳጅ አፈጻጸማችን ሁሉንም ወደ ትክክለኛው ቦታ መመለስ እንደሚቻልም እናውቃለን።
ማንም በነዳው ቁጥር በአጉራ ዘለልነት እኛ ላይ ቃታ ለመሳብ የሚዳዳው የትኛውም ሃይል በአሳፋሪ ድርጊቱ ብናዝንም የመጨረሻ ውጤቱ ምን እንደሆነ ከልምዳችን አሳምረን እናውቃለን።
አሳዛኙ ነገር ከትላንቱ ምስቅልቅል ቀውስ እና ኪሳራ ካተረፈልን ችግር መማር ያልቻሉ “ጦር አውርድ” ባዮች ምን ያህል ለህዝብና ለሀገር ግድ እንደሌላቸው እየታወቀ፤ የእነዚህ እኩያን ተከታይ ጋሻ ጃግሬ መኖሩ ነው።
የፈለገውን ዓይነት ጭምብል ይልበስ በሀገር ህልውናና በህዝብ ሰላም ላይ ተረማምዶ የፍላጎቱን ቅንጣት ማሳካት አይችልም።
እኛን በእጅጉ የሚያሳዝነን የውጭ ሃይሎች ተጋላቢ ፈረሶች፣የስልጣን ጥማተኛ ጃስ ተብዬዎች ዓይናቸውን ጨፍነው በሚለኩሱት እሳት የህዝብን ሰላም ከማወክ አልፈው ማህበራዊ እረፍት ሲነሱት ነው።ያ እኛን ያመናል።
ምንም ሆነ ምን ግን በመስዋዕትነታችን ዋጋ የህዝባችንን ሰላም የሀገራችንን ህልውና አስጠብቀን ምርቱን ከግርዱ በለየ አስተውሎታዊ ግዳጅ አፈጻጸም ኢትዮጵያችንን አጽንተን ከነክብሯ እናስቀጥላታለን።
ለእኛ ከኢትዮጵያ የሚበልጥብን አንዳችም እሳቤ የለም።
ሁሉም ነገር የሚያምረው በሀገር ነውና ስለሀገር መቤዛችን የማይቆም ግዴታችን ነው።
ለማንኛውም ሁሉም በጎ ይሆናል።የሚያሳስበን የምንከፍለው ዋጋ አይደለም።የሀገርና ህዝብ ሰላም እንጂ።
በሀገርና በወገን ያሴረ ስሜት የሚነዳው አጉራ ዘለል ጊዜያዊ እውክታ ይፈጥር ይሆን እንጂ የትም እንደማያደርሰው ራሱም ጠንቅቆ ያውቀዋል።
“እኛን የሚያሸንፈን ማንም ሳይሆን በነፍሳችን ልናጸናት የቆምንላት ኢትዮጵያችን ፍቅር ብቻ ነው።”
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት
“
